Fana: At a Speed of Life!

በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሰጡት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

የሀገራችን ህዝቦች ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት በጋራ እየታገሉ መስዋእትነት እየከፈሉ በጋራ ተጉዘዋል፤ አሁም በመጓዝ ላይ ይገኛሉ።

የህዝቦች የጋራና ትግልና መስዋእትነት ፍሬ አፍርቶ ሃገራችን የለውጥ ሂደት ውስጥ ገብታለች። ሆኖም በዚህ የለውጥ ሂደት በህዝቦች ትግል ድል የተነሱት ጨቋኝ ክንዳቸው እንዲሰበሰብ፣ የብዝበዛ መረባቸው እንዲበጣጠስ የተደረገው ሴረኛው የወያኔ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ላደረሳቸው ጥፋቶች መፀፀትና መታረም ሲገባው አሁንም የተካነበትን ሴይጣናዊ የተንኮል ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

ይህ ቡድን እንደለመደው ህዝብን ከህብ በማጋጨት ደም በማፋሰስ፣ በሚፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከቻለ ከተገፋበት የማዕከል ስልጣን መመለስ ካልቻለ የሚመቸውን አሻንጉሊት መንግስት ለማቋቋም በተለመደው አይነ ደረቅነቱን የቀን ቅዠት ውስጥ በመግባት ሌት ተቀን ሴራ በመጎንጎን ላይ ይገኛል።

ከወያኔ እኩይ የሴራ ድርጊቶች መካከል ዋነኛው ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ህዝብ ከህዝብ በማጋጨት በንጹሃን ደም መነገድ ነው።

በተለይም ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር መሞከር የሰርክ ተግባሩ ነው።

ይህ ሙከራዉ አልሳካለት ሲለዉ የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድንን በማስታጠቅ የሎጀስቲክና የፋይናን ድጋፍ በማድረግ በትሮይ ፈረስነት በመጠቀም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማስፈጸም የሃገራችንን የለውጥ ተስፋ ለማጨለም እየተፍጨረጨረ ይገኛል።

አሸባሪው የኦነግ ሸኔ ቡድን ባለፉት ሁለት አመታት በህዝብና በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ትብብር እየተወሰደ ባለው እርምጃ በከፍተኛ ሁኔታ አከርካሪው ተመትቶ በመንኮታኮት ላይ ይገኛል።

ይህ በህዝብና በጸጥታ አካላት ክፉኛ እየተመታ ያለው ቡድን ተስፋ ወደ መቁረጥ በመግባቱ, እንዲሁም ከወያኔ የሚሰጠውን ተልዕኮ በመውሰድ ሰላማዊ ዜጎችን አርሶ አደሮችን በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራሮች ላይ የሽብር ጥቃት ወደ መሰንዘር ተሸጋግሯል።

በትላንትናው እለት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለው ቀበሌ ዜጎቻችን ላይ የሽብር ጥቃት በማድረስ በሰው ህይወት እና አካል ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

በዚህ የሽብር ጥቃት ዉድ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅኩ የተፈጠመውን፤የሽብር ጥቃት አጥብቄ አወግዛለሁ።

በዚህ አጋጣሚ በኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው ውጤታማ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋግጥ እወዳለሁ።

እንደዚህ አይነት የፈተና ወቅት የህዝቦችን ወንድማማችነትና በጽናት አብሮ በመቆም ፈተናን የማለፍ ልምድን ያጠናክራል እንጂ ጠላት እንደተመኘው ህዝቦችን የሚያባላ ፈጽሞ አይሆንም፡፡

እንደ መንግስትም አስፈላጊዉን መስዋዕትነት በመክፈል የህዝቦችን ወንድማማችነት እና የኢትዮጵያን አንድነት የማስቀጠል ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ ሽብር እና የጥፋት ሴራ ኢትዮጵያ አትፈረስም።

ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርእስ መስተዳድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.