Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት በምዕራብ ወለጋ ዞን በዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በምዕራብ ወለጋ ዞን በዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ።
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የአማራን ህዝብ ማህበራዊ እረፍት በመንሳት የራስን ሰላም ማግኘት አይቻልም!
ላለፉት 40 ዓመታት በተለይም ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ፤ በአማራ ህዝብ ላይ ማንነትን መሰረት ያረደጉ ጥቃቶች ሲሰነዘሩበት ቆይተዋል፡፡
በዚህ ችግር ዋነኛው ተጠቂ ከክልሉ ውጭ ነዋሪ የሆነው ወገናችን ነው። ለዚህ ጥቃት ያበቃው መሰረታዊ መንስኤው ደግሞ የትህነግና መሰል ኃይላት የአማራን ህዝብ በተመለከተ የዘሩት አማራ ጠል ትርክት ሲሆን፤ የዚህ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች አማራን ለማጥቃት በትር ሆነው አገልግለዋል። በኢትዮጵያ የመንግሥት ምስረታ ሂደት ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው አማራ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ሁሉ ሀገሬ ብሎ ለረዥም ዘመናት የኖረ በመሆኑ የህዝባችን አሰፋፈር እና የአኗኗር ዘይቤው ለጠላቶቹ የበለጠ ተጋላጭ አድርጎታል፡፡
የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ጽኑ እምነት ያለው ህዝብ በመሆኑ፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል መኖርና ተዘዋውሮ የመስራትና ሀብት ማፍራት ‘ሕገ-መንግስታዊ መብቴ ነው’ ብሎ ያምናል፡፡በዚህ እምነቱ የተነሳም፤ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ይኖራል፤ ተዘዋውሮ ለመስራትና ሀብት ለማፍራ የሕይወት ትግል ያደርጋል፡፡
ይሁን እንጅ ትህነግና መሰሎቹ በዘሩት የተዛባ ትርክት የአማራ ህዝብ እረፍት አጥቷል፤ በየወቅቱና በየአካባቢው ይሰደዳል፤ ንብረቱ ይዘረፋል፤ አለፍ ሲልም የቡድን ጥቃት ይፈፀምበታል። ይህ ችግር በድርጅት የውስጥ መተጋገልና በኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ መስዋዕትነት ትህነግ ከማዕከላዊ ሥልጣኑ ከተነቀለ በኋላ የአማራው መጠቃት በከፋ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከሥልጣን ለመነቀሌ የተቃውሞ ኃይል ምንጭ ነው ብሎ የሚያምነውን የአማራ ሕዝብ፣ ከትላንት በቀጠለ ጥላቻው ዛሬም አማራን ማጥቃት የበቀልና የሥልጣን መመለሻ የቀውስ ሃዲድ አድርጎ ይቆጥረዋል።
ይህ የሚያሳየው፣ ትህነግ እንደ ድርጅት ህልውናው እስከቀጠለ ድረስ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው መፈናቀል፣ ግድያና ጭፍጨፋ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን ነው፡፡ ይሄን የምንለው የአማራ ህዝብ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎቹ አገራችን አካባቢዎች፤ ዋጋ እየከፈለ ያለው በትህነግ የእጃዙር ጥቃት መሆኑን ከክትትልና መረጃዎች እንዲሁም ከሁኔታ ትንተናዎቻችን ተነስተን ነው። ኦነግ ሸኔም ይሁን ሌሎች ፀረ-ሕዝብ የሆኑ ኃይሎች ያለ ትህግ የፕሮፓጋንዳ፣ የትጥቅና የፋይናንስ ድጋፍ ያን ያክል ለፌደራሉም ሆነ ለክልላዊ መንግሥታቱ አስቸጋሪ ሆነው አማራን ባላፈናቀሉ፣ ባለሰደዱና ባልጨፈጨፉ ነበር፡፡ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አማራ ለገባንበት የጥቃት አዙሪት ምንጩ የመቀሌው ግዞተኛ ቡድን ነው።
በትላንትናው ምሽት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዘርን መሠረት ያደረገ የአማራን የቡድን ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠናል። የጥቃቱን መጠንና ዝርዝር ሁኔታዎች ከፌዴራሉና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር እያጣራን ሲሆን፤ በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት የአማራ ህዝብና ድርጅታችን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ክፉኛ አዝኗል፤ ተቆጥቷል፡፡ በመሆኑም ይህ ድርጊት የሚወገዝ ከመሆኑም በላይ አጥፊዎቹ እንደየስራቸው በህግ አግባብ ሊዳኙ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡
ስለሆነም ከዚህ በታች የሚከተሉት አካለት ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን፦
1) የፌደራሉ መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ በየ አካባው እየደረሰ ያለውን ተደጋገሚ ዘር ለይቶ የማጥቃት ወንጀል ዋነኛ የብሔራዊ ደኀንነት አደጋ አድርጎ ሊወስደው ይገባል። ስለሆነም የኢፌዴሪ ብሔራዊ የደኀንነት ምክር ቤት የአደጋውን መጠንና ቀጠናዊ መዘዝ በማጤን ዘርን መሠረት ያደረገው የአማራ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤ ስለ ጥቃቱም ዝርዝር መረጃ ለመላ ኢትዮጵያዊያን እንዲሰጥ፤ በአማራው ጥቃት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ የጥፋት ኃይሎች ላይ ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እንጠይቃለን፤
2) የአማራ ህዝብ የሚኖርባችው ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የምትገኙ የፖለቲካ አመራሮችና የጸጥታ አካላት፣ እናንተንና የአካባቢውን ወንድም ህዝብ አምነው አገር አለን ብለው፤ ሕግና ሥርዓት አለ በሚል ኢትዮጵያዊ መተማመን ከናንተው ጋር ለዘመናት የኖሩትን የአማራ ተወላጆች ከመቸውም ጊዜ በላይ ጥበቃ እንድታደርጉላቸውና ሕዝባዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤
3) በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ተከታታይ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ፤ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ አማራን በየ አቅጣጫው በመውጋት በንጹሃን ደም የፖለቲካ ቁማር የሚሰራው የመቀሌው ግዞተኛ የትህነግ ቡድን በመሆኑ፣ ይህ ኃይል የብሔራዊ ደኀንነታችን የስጋት ምንጭ ከመሆን አልፎ የሽብርና የቀውስ ማዕከል ስለሆነ ለኢትዮጵያና ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም ሲባል ከመለሳለስና ከመሸከም ፖለቲካ ወጥቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስርአት እንዲያስይዝ ለማድረግ ጊዜው አሁን ስለመሆኑ እናስረግጣለን፤
4) የኢትዮጵያ ዘብ የመሆን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ ያለባችሁ የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌደራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አካላት የአማራ ህዝብና ሌሎች ብሔሮች በማንነታቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ስትከፍሉት የቆያችሁትን መስዋዕትነት መቼም አንዘነጋውም። ዛሬም ከሀገራዊ ለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ጸረ-ሕዝብ የሆኑ ኃይሎች አማራውን ዘሩን መሰረት አድርገው ጥቃት እየተፈጸሙበት መሆኑን አውቃችሁ፤ በየአካበቢው ለሚኖረው አማራ ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ በመስጠት፤ ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኳችሁን እንድትወጡ በድጋሚ እናሳስባለን፤
5) የአማራ ህዝብ፣ ምሁራን፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ፦ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የረዥም ጊዜ የተዛባ ትርክት ውጤት መሆኑን በመገንዘብ፤ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት፣ ለሦስት አስርታት የገጠመንን መዋቅራዊ ማነቆ ለመቅረፍ በሚመጥን ልክ የመፍትሄ ሃሳብ በማመንጨት የበኩላችሁን እንድትወጡና በጋራ በመቆም የአማራ ህዝብ ከተደቀነበት የህልውና ስጋት እንድታደገው ‘የአማራ አንገቱ አንድ ነው’ በሚል ወገናዊ ጥሪያችን እናቅርብላችኋለን፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በዘለቄታዊ መፍትሄው ላይ እንደ አማራ ለመምከር በቅርቡ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሕዝብ መድረክ የምናዘጋጅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
የአማራን ህዝብ ማህበራዊ እረፍት በመንሳት የራስን ሰላም ማግኘት አይቻልም!
አማራን ዘሩን ለይቶ በማፈናቀልና በመግደል ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም!
ክብርና ሞገስ በአማራነታቸው መስዋዕት ለሆኑ ወገኖቻችን!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ!
ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.