Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት ማዘናቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘናቸውን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት ፅሁፍ የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው መነሳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ መሆኑን በማንሳትም የሕዝቦችን ቅስም መስበር አንደኛው ዒላማቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡

ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ መሆኑንም አውስተዋል።

መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ እርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ መቆየቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ያለፈው ሥርዓት የፈጠራቸው ቀዳዳዎች በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ እንዳልተቻል አንስተዋል፡፡

የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝቦች ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን ገልጸዋል፤ ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ የሚሰብር መሆኑን በመጥቀስ።

ይህ ግን ከመንገድ ወደኋላ፣ ከተያዘው ግብ ወደ ሌላ እንደማያደርግ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም” ብለዋል።

“ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናልም” ነው ያሉት።

መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ እንደሚነቅለው በማውሳትም፥ የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተው እርምጃም እየወሰዱ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም የሕዝቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፣ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን እርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.