ኮቪድ 19ኝን በመከላከል ሃገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽዕኖንና ስርጭትን በመከላከል ሃገራዊ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
መመሪያው ሁሉንም የምርጫ ሂደቶች ያካተተ መሆኑንም ነው የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ያስታወቁት።
በመመሪያው ዝግጅት ላይ የህግ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ምክረ ሃሳብ ተካቶበት እንደሚዘጋጅም ነው የተገለፀው።
ለመመሪያው ዝግጅት ግብአት ለማሰባሰብና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማካተት ዛሬ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር መክሯል።
በምክክሩ በተለይ ፓርቲዎቹ ተንቀሳቅሰው በሚሰሩባቸው ገጠራማ አካባቢዎች በወረርሽኙ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ደካማ መሆኑንና የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ አለመሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።
በተለይ የምርጫው ጊዜ ሲቃረብ የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴም ስለሚጨምር ከወዲሁ የግንዛቤ ማስጨበጫና ፈጣን የመረጃ ፍሰት ዘዴ ሊኖር ይገባልም ነው ያሉት።
በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ስድስተኛው የሃገራዊ ምርጫ ሰሌዳ ረቂቅም በውይይቱ ቀርቧል።
በዚህም የመራጮች ምዝገባ ከጥር ወር መጨረሻ እስከ የካቲት ወር መጨረሻ፣ የእጩዎች ምዝገባ ከየካቲት መጀመሪያ እስከ የካቲት አጋማሽ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፓርቲዎች ቅሬታና አቤቱታቸውን የሚያቀርቡበት ወቅት ከየካቲት ወር መጀመሪያ እስከ የካቲት መጨረሻ ለማድረግ ታቅዷል።
በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ከየካቲት ወር መጨረሻ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ እንዲሁም ድምፅ አሰጣጥ ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ ይሆናል።
ከምርጫው ወቅት ጸጥታ ጋር በተገናኘው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው የሰላም መደፍረስና የዜጎች ህይወት መጥፋት ሊገታ ይገባልም ብለዋል።
በምርጫው ሂደት ላይም እንቅፋት እንዳይፈጥር መንግስት ከወዲሁ መፍትሄ ሊያበጅ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሰላማዊት ካሳ