Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በጥፋት ሀይሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው ወንጀል ማዘኑን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ትናንት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በጥፋት ሀይሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው እጅግ አስከፊ ወንጀል ማዘኑን ገልጿል።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ በኖረባቸው ረጅም ዘመናት ውስጥ ክፉና ደጉን አብሮ አሳልፏል፤ በታሪክ የገጠሙትን ችግሮች ሁሉ በወንድማማችነት እና በአንድነት ተሻግሯል ብሏል።

ከምንም በላይ ደግሞ ለ27 ዓመታት በህወሀት ቡድን የተጫነበትን አስከፊ የግፍ ስርዓት በአንድነት ክንዱ ታግሎ በመጣል የለውጥ መንገድ ጀምሯል ነው ያለው።

ይህንን የህዝብ ድል ለመቀልበስ ትናንት ህዝቡን ሲገርፍ እና ሲያንገላታ የነበረው ቡድን ከተላላኪዎቹ ጋር እየሞከረ ነው ያለው መግለጫው ላለፉት ሁለት ዓመታት በኦነግ ሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ሲፈፀም የነበረው ግፍ የዚህ ሙከራ አካል እንደሆነ እና በዚህ ውስጥ የዜጎች ህይወትና ንብረት መጥፋቱን አስታውሷል።

ትናንትና ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድን ከህወሀት በተቀበለው ተልዕኮ በንፁሃን ዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ ወንጀል መፈፀሙን ያመለከተው የፓርቲው መግለጫ ድርግቱ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ወንጀል ነው ሲል ገልጿል።

የዚህ ወንጀል ዓላማ ህዝብን በህዝብ ላይ በማነሳሳት ሀገርን ማፍረስ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ከግድያው በስተጀርባ ያለውን ሴራ ስለሚያውቅ የጥፋት ሀይሎቹ ህልም ፈፅሞ አይሳካም ብሏል።

በመግለጫው ይህ አስከፊ ወንጀል የእነሱን ሞት ከማፋጠንና የሠላም ምዕራፍን ከማቅረብ የዘለለ ትርጉም የለውምም ነው ያለው።

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በጥፋት ሀይሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው እጅግ አስከፊ ወንጀል በጣም አዝነናል፤ እነዚህን ፀረ-ሰው ሀይሎች መስመር ለማስያዝ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ አመራሮቻችን እና አባላቶቻችን አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል እንደሚሳተፉ በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን በማለት በመግለጫው አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.