ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን እንደማይችል የብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የላከው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል
ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በሃገራችን እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር ለማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም በሃገራችን ህዝቦች ዘንድ ትልቅ ተስፋና መነቃቃት መታየት የጀመረ ሲሆን ሃገራችን በሰላማዊ፣ በሰለጠነና በሰከነ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሚመራ ነጻ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር እንደምትችን የተስፋ ብርሃን የታየበት የፖለቲካ ሪፎርም ሲካሄድ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት የማይዋጥላቸውና ግድያን፣ ማፈናቀልን፣ ንብረት ማውደምንና ንጹሃን ዜጎችን ማሸማቀቅን እንደ ዋነኛ የስልጣን ምንጭ አድርገው የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን መረጋጋትና የዜጎቿን ሰላም የማይፈልጉ ሃይሎች ቅንጅት በመፍጠር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸውን ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ኢላማ በማድረግ ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህ እኩይና ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ የጥፋት ተግባራቸው ባለፉት አመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ንብረት እንዲወድምና ዜጎች የሰላም ስሜት እንዳይሰማቸው ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በተለይም ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እና በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ የበርካታ ንጹሃንን ህይወት የቀጠፈ ጨካኝ የሽብር ተግባር ተፈጽሟል፡፡ የንጹሃንን ደም በማፍሰስ ስልጣን መያዝን ካልሆነም ሃገርን መበታተንን ዋነኛ ዓላማቸው አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ኦነግ ሸኔ የተባለው አሸባሪ ቡድን በሀይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ከሚፈልጉ ካልተሳካላቸውም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን ከሚሰሩ ተቀናጅተውና በትጥቅ ተደግፈው በትናንትናው እለት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለው ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት የዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካታ የአካል ጉዳትም ደርሷል፡፡
ይህ የሽብር ጥቃት ፍጹም ሰላማዊ በሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተቃጣ መሆኑ አጥፊ ቡድኑ የሚከተለው መንገድ ምን ያህል ያልሰለጠነ፣ ኋላ ቀርና ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን ለዓለም ህዝብ ያጋለጠበት ነው፡፡
በዚህ አረመኔዊ ተግባር ህይወታቸውን ላጡ ዜጎቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለተጎጂዎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን እንመኛለን፡፡ መንግሥት እነዚህን ነብሰ ገዳዮች ከያሉበት አድኖ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እያረጋገጥን የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው የሃገራችን ህዝቦች የንጹሃን ዜጎችን ህይወት ያጠፉና አካል ያጎደሉ ሽብርተኛ ቡድኖችን አድነን እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ህብረ- ብሄራዊ ፌዴራላዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገው እርምጃ ውስጥ ከጎናችን በመሆን አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት
ጥቅምት 23 ቀን 2013