የሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡
ሲኖዶሱ ከጥቅምት 11 ቀን ጀምሮ ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ይበጃሉ ያላቸውን ውሳኔዎች ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
በዚህም ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የቀረበው የጉባዔ መክፈቻ ንግግር የበጀት ዓመቱ የሥራ መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለምልዓተ ጉባዔው ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት የ39ኛው አጠቃላይ የሰበካ ጉባዔ የጋራ መግለጫ ጉባዔው ተቀብሎ በማጽደቅ ለሚመለከታቸው ሁሉ ተላልፎ በሥራ እንዲተረጎም ወስኗል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ችግርን አስመልክቶ ጉባዔው ሰፊ ውይይት ያደረገ ሲሆን፥ በቤተ ክርስቲያኗ አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ ውሳኔ ማሳለፉን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ስርጭት ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዚሁ ጋር በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያን ወገኖች ላይ ለደረሰው ጥፋት ለወደፊት የሕግ ክትትል በማድረግ ችግሩን የሚከላከሉ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
ከዚህ ባለፈም በጉባዔው ላይ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይና የሰላም ሁኔታ ላይ በመወያየት እርቅና ሰላም ማምጣት አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የእርቅና የሰላም ሂደቱን የሚያስፈጽሙ ብፁዓን አባቶችን በአስታራቂነት ሰይሟል፡፡
ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አካባቢያዊ ጦርነት እንዲነሣ ያስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ወይም በሞግዚትነት ለማስተዳደር የተደረገ ሙከራ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአጽንኦት ተቃውሞታል፡፡
የዓለም መንግሥታትና ሕዝቦችም እንዲህ ዓይነቱን ትንኮሳ እና የቅኝ ግዛት ፍላጎት እንዲቃወሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡