Fana: At a Speed of Life!

የፕሮጀክቶች መጓተት በ4 ቢሊየን ብር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እስከ 16 ቢሊየን ብር ወጪ እንዲጠይቁ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሮጀክቶች አስተዳደራዊ አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት በ4 ቢሊየን ብር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እስከ 16 ቢሊየን የሚጠጋ ብር እንደሚጨርሱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

ቋሚ ኮሚቴው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማቱን የ2013 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

በግምገማው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራትና  ቋሚ ኮሚቴው የሚሰጣቸውን ግብረ መልሶች በግብአትነት ከመጠቀም እንዲሁም፤ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ወቅታዊ አደጋዎችና ችግሮችን ታሳቢ አድርጎ ከማቀድ አኳያ ውስንነት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር አንስቷል፡፡

ከአፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን ባሻገር አብዛኛዎቹ መሰረተ ድንጋይ ከማስቀመጥ ያለፈ ተጠናቀው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሲያደርጉ አለመታየቱን የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተው በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለውሃ ልማት ፈንድ የሚሰጠው ተዘዋዋሪ ብድር እንዲመለስ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ባለመመለሱ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንቅፋት መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገነቡ ንዑስ ጣቢያዎች የመብረቅ መከላከያ ባለመሰራቱ አብዛኛዎቹ ከሳምንት በላይ እያገለገሉ አለመሆኑም ተነስቷል።

በመሆኑም በ2013 በጀት ዓመት ችግሩ ታሳቢ ተደርጎ መፍትሄ ሊቀመጥለት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው መግለፁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.