Fana: At a Speed of Life!

በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ የተፈፀመው ጥቃት በኦነግ ሸኔ መፈፀሙ ተረገጋጧል – የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ የተፈፀመው ጥቃት በኦነግ ሸኔ መፈፀሙን እና የህወሓት ድጋፍ እንዳለው ማረጋገጡን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የተፈፀመው ጥቃት በኦነግ ሸኔ ፈፃሚነት በህወሓት ድጋፍ ሰጭነት ስለመፈፀሙ ፖሊስ አረጋግጧል ብለዋል።

ኦነግ ሸኔ ከለውጡ በፊት በሽብርተኝነት ተፈርጆ እንደነበር ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ ባለፉት ሁለት ዓመታትም መሰል ጥቃቶችን እየፈፀመ መቆየቱን ተናግረዋል።

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ትግራይ መቐለ እየተመላለሱ ስልጠና ያገኙ እንደነበር ከተያዙ አካላት ማወቅ መቻሉን፣ የጦር መሳሪያ እና የፋይናንስ ድጋፍ በህዋሃት ይሰጥ እንደነበረ መታወቁ፣ ድምፀ ወያኔ እና ኦ ኤም ኤን ሚዲያን በመጠቀም የጥቃት ቅስቀሳ ያደርግ የነበረ መሆኑን የሁለቱን አካላት ግንኙነት የሚያሳይ ከመሆን ባሻገር በኦነግ ሸኔ ለመፈፀሙ ፖሊስ በማረጋገጫነት የያዘው ጉዳይ ነው ብለዋል።

በጥቃቱ እስካሁን 34 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ፣ የደረሱበት ያልታወቀ 11 ግለሰቦች እንዳሉ የገለፁት ኮሚሽነሩ፣ ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ የአርሶ አደር መኖሪያ ቤቶችና አንድ ትምህርት ቤት መቃጠሉን ገልጸዋል።

አካባቢዎቹን የማረጋጋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፥ ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

ህዝቡም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ሊያሳይ ይገባልም ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑን ከስሩ ለማፅዳት ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራም አውስተዋል፡፡

በሀብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.