Fana: At a Speed of Life!

በለውጡ ደስተኛ ያልሆኑ አካላት እየፈጸሙት ያለው ግፍና በደል ሊቆም ይገባል – የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በለውጡ ደስተኛ ያልሆኑ አካላት እየፈጸሙት ያለው ግፍና በደል ሊቆም እንደሚገባው የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የፖቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ በፓርቲው እቅድ አፈጻጸምና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አቶ አብርሃም በሰጡት መግለጫ ለውጡ ተደናቅፎ እንዲቆም የሚፈልጉና በለውጡ ደስተኛ ያልሆኑ አካላት በህዝብ ላይ እየፈጸሙት ያለው ግፍና በደል ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ንፁሃንን ስብሰባ በመጥራት በአሰቃቂ ሁኔታ ህጻናት፣ ሴቶችና እናቶች ሳይቀር መገደላቸውን አብራርተው ይህንን ሰብዕና የጎደለው አሰቃቂ ድርጊት የፈጸሙ ኃይሎች የፈጸሙትን እኩይ ተግባር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ህዝብ በሚኖርበት ሁሉ በሰላም እንዲኖር፣ ለሃብትና ንብረቱም ዋስትና እንዲረጋገጥለት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡

እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል ኦነግ ሸኔና ህወሃት በጥምረት እየፈጸሙት መሆኑን የተናገሩት አቶ አብርሃም፤ በመንግስት መዋቅር ውስጥም የህዝቡን ጥቅም ወደ ጎን በማለት የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ አካላት መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህን አካላት በመታገል ችግሩን ለመፍታት መንግስት ህግን የማስከበርና መዋቅሩን የማጥራት ስራ በሰፊው እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

እየደረሰ ያለው ግፍ በአጭር ጊዜ እንዲቆም በትኩረት እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ከጥቅምት 23 እስከ ጥቅም 26 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በውይይቱ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና መፍትሔዎች ዙሪያ የሚመከር መሆኑን አቶ አብርሃም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.