የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ አዋሬ ገበያ አካባቢ የተነሳው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ውሏል

By Tibebu Kebede

November 04, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሬ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተነሳው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ከሌሊቱ 10 ሰአት አካባቢ የተነሳው የእሳት አደጋ በአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች፣ ፖሊሶች እና የአካባቢው ወጣቶች በቁጥጥር ስር መዋሉን የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ ተናግረዋል፡፡

የእሳት አደጋው መንስኤ እና ያደረሰው ጉዳት በፖሊስ እየተጣራ መሆኑም ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከየካ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው የጉዳቱን መጠን በመመልከት ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች አጽናንተዋል፡፡

በእሳት አደጋው የደረሰውን ጉዳት እየተጣራ መሆኑንም ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡