ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በትኩረት መስራት ይገባዋል- አቶ ርስቱ ይርዳ
አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በትኩረት መስራት ይገባዋል ሲሉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ተናገሩ፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ÷ ህወሀት ባለፉት አመታት ሀገሪቱን እየመራ በነበረበት ወቅት በሀገሪቱ በፖለቲካው ፣በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
ህወሀት መንግስት ከዚህ ቀደም ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋት እና ትርምስ እንዲኖር ሲሰራ እንደነበር ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን ደጀን በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሠንዘር እና ሀገሪቱን በሀይል ለመናድ እና በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ በማሰብ ህወሀት እያደረገ ያለውን ጥረት መንግሥት ሁኔታውን በመቆጣጠር ላይ ነውም ነው ያሉት ፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም የጥፋት ሀይሎች ብሄርን ከብሄር በማጋጨት በየአካባቢው እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን ሽፋን በማድረግ እንዲሁም የሽብር ተግባራትን በመፈጸም ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ አጀንዳ ቀርጸው ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ከግምት በማስገባት ህብረተሠቡ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡
ሀገሪቱን ከአደጋ እና ህዝባችንን ከጥቃት መከላከል ላይ ማተኮር ይገባናል ያሉት አቶ ርስቱ ለዚህ ደግሞ አመራሩ የጸጥታ መዋቅሩ እና መላው ህብረተሰብ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡
በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የክልሉ መንግሥት እንደሚያወግዝም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
ሀገሪቱ አንድነቷ ተጠብቆ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ይሰራል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የሚዲያ አካላትም ለህብረተሰቡ ትክክለኛውን መረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ርስቱ÷ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚሰሩ አክቲቪስቶች ሀገርን እና ህዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።