Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ህዝብ በስሙ ሲነግዱ የነበሩ የህወኃት አመራሮችን በማጋለጥ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆም ትዴፓ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የትግራይ ህዝብ በስሙ ሲነግዱ የነበሩ የህወኃት አመራሮችን በማጋለጥ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ጥሪ አቀረበ።
 
በህወኃት ውስጥ ያሉ ቡድኖች በሕገ-መንግሥትና በፌዴራል ሥርዓት አልገዛም በማለት ከመሀል አገር ሸሽቶ መቐለ ከመሸገ ወዲህ የትግራይ ወጣቶችን እየሰበሰበ ”በልዩ ሀይል”ሥም ሲያደራጅ፣ ሲያሰለጥንና ሲያስታጥቅ መክረሙንም ትዴፓ በመግለጫው አመልክቷል።
 
አመራሮቹ እነዚህን ወጣቶች በመላ ሃገሪቱ በማሰማራት በንፁሐን ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸምና በኢትዮጵያ አለመረጋጋት እንዲነግስ በማድረግ ወደ ሚናፍቁት ስልጣን የመመለስ ፍላጎት አላቸው ብሏል።
 
ጥቂት የህወኃት ቡድኖች በሃገር አንድነትና በህዝቦች ህልውና ላይ እየፈጸሙ ያለውን የሽብር ጥቃት መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሲል በሆደ ሰፊነት ማለፉ ለህዝቡ ያለውን ወገንተኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቅሷል።
 
”የህወኃት አመራር ለ29 ዓመታት መላው የኢትዮጵያ ህዝብን ረግጦና በዝብዞ ገዝቷል” ያለው መግለጫው የትግራይ ህዝብ ያተረፈው የእነርሱን መጥፎ ስም ብቻ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጠው።
 
የትግራይ ህዝብ መከራ እንዲያበቃ በስሙ ሲነግዱ የነበሩ የዴሞክራሲ፣ የሠላምና የአንድነት ጠላት የሆኑት የህወኃት አመራሮችን በማጋለጥ ወገንተኝነቱን ካረጋገጠው የመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም እንደሚገባም አሳስቧል።
 
መንግሥትም ይሁን የአገር መከላከያ ሠራዊት ለትግራይ ህዝብ ሲባል ያሳየውን ጥንቃቄና ሆደ-ሠፊነት የሚደገፍ ቢሆንም፤ የህወሓት አመራር ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰዱ ለአገር አንድነትና ለወገን አለኝታነት ሲባል የሚደገፍ ነው ብሏል ትዴፓ በመግለጫው።
 
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ህዝብ የህወሓት አመራር ክፉ አገዛዝ ሠለባ መሆኑን በመገንዘብ በጋራ ትግል ለጋራ ድል ለመብቃት ለሚደረገው ጥረት ተባባሪ እንዲሆን ትዴፓ ጥሪ ማቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል።
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.