በአሶሳ ከተማ በድብቅ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በህወኃት ውስጥ ካለ ቡድን ጋር ድብቅ ግንኙነት በመፍጠር በአሶሳ ከተማ ጥፋት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንደሆኑ የተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ዛሬ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱላዚዝ መሐመድ አስታወቁ።
ግለሰቦቹ በአሶሳ ከተማ ኢንቨስትመንትን ሽፋን በማድረግ ጥፋት ለመፈጸም ከህወኃት ድብቅ ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ብለዋል ኮሚሽነሩ።
ከዚህ ቀደም በክልሉ መተከል ዞን የተፈጸመውን ጥቃት ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፤ ግለሰቦቹ ይህንን ጥፋት ዳግም ማስቀጠል ዋነኛ ግባቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ግለሰቦቹ “ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ መንግስት የለም” በሚል ከሃገር ውስጥ እና ከውጪ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ከሚሠራው የጥፋት ኃይል ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የፖሊስ ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡
ግለሰቦቹ የአካባቢውን ወጣቶች በድብቅ በመመልመል ተጨማሪ ግጭት ለማስከተል ገንዘብ እና ሌሎችንም ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ እንደነበር የሚያመላክት መረጃ ፖሊስ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም የክሉልን መንግስት ውጥረት ውስጥ በማስገባት ስልጣን ማስለቀቅና በአካባቢው ትርምስ እንዲፈጠር ማድረግ የግለሰቦቹ ፍላጎት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
“ይህ ሁኔታ እንዲፈጸም የክልሉ ጸጥታ ኃይል በፍጹም አይፈቅድም” ያሉት ኮሚሽነሩ መንግስት መኖሩን ብቻ ሳይሆን በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድም ጭምር የህዝብ ደህንነት በማስጠበቅ ሠላም ማረጋገጡን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ትብብሩን እንዲያጠናክርም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።