Fana: At a Speed of Life!

ከህወሃት የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው በጋምቤላ ክልል ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት አሲረው ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት ከህወሃት የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው በጋምቤላ ክልል ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት አሲረው ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ጸጋዬ መብርሃቱ (ካህሳይ)፣ ገብረማሪያም አናንያ፣ ዋስትና ተሾመ (ጃል ሴና)፣ አብርሃም መሃሪ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ (ባሌስትራ) እና ሌሎች 19 የህወሃትና የኦነግ ሸኔ የጥፋት ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።

በክልሉ ብሄር ብሄረሰቦችን በማጋጨት አካባቢውን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ አሲረውት የነበረው ሴራ ከሽፎ ግለሰቦቹም በቁጥጥር ስር ውለዋልም ነው ያለው።

በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ተፈጽሞ የነበረ ተመሳሳይ ጥፋት በዚያው በክልሉ ውስጥ በአሶሳና ካማሼ ዞኖች ብሔር ብሄረሰቦችን በማጋጨት አካበቢውን የትርምስ ቀጠና በማድረግ እልቂት ለመፈጸም የህወሃት የጥፋት ቡድን አባል ከሆነው አባይ ጸሃዬ ተልዕኮ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ዮሃንስ ግርማይና ርዕሶም ግርማይ የተባሉ ግለሰቦች ከሌሎች 20 ግብረ አበሮቻቸው ጋር በቁጥር ስር መዋላቸውንም ገልጿል።

በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እነዚህን የጥፋት ሃይሎች በቁጥጥር ስር ለማዋልና ሴራቸውን ለማክሸፍ በተካሄደ ዘመቻም የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የየክልሎቹ የጸጥታ አካላት በቅንጅት መሳተፋቸው ተገልጿል።

በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ጥፋት ለመፈጸም ተልዕኮ ወስደው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የጥፋት ሃይሎች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው ብሏል።

አጠቃላይ የጥፋት ሴራውን በማክሸፍ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተም በተከታታይ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.