Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ማብራሪያ ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርምሮ ማጽደቁን ተከትሎ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ምክንያት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስተባብረው ግብረ ሃይል የተቋቋመ ሲሆን ግብረ ሃይሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የሚኖረውን ስልጣንና ተግባር በዝርዝር ተቀምጧል፡፡

በዚህ መሰረት በመጀመሪያ በተቀመጠው በትግራይ ክልል ላይ ተፈጻሚ በሚሆነውና ለስድስት ወር በሚቆየው በዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ግብረ ሃይሉ በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሰብሳቢነት የተቋቋመ ሲሆን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ተናግረዋል፡፡

ግብረ ሃይሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፋትም ሆነ የማጥበብ ስልጣን የተሰጠው ሲሆን፥ ማንኛውንም የፀጥታ ሃይል በማስተባበር በአንድ ዕዝ ስር እንዲመራ ማድረግ ይችላልም ነው የተባለው፡፡

በትግበራው ወቅትም ተልዕኮውን ተፈጻሚ በሚያደርግበት ጊዜ አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ድንጋጌዎች ማውጣትም ሆነ መተግበርም ይችላል ነው ያሉት፡፡

በመደበኛ የዜጎች መብት ሳይገደብ አዋጁ በተጣለባቸው አካባቢዎች ላይ ተልዕኮውን ማስፈጸም የሚያስችለውን እርምጃ መውሰድም ይችላል ነው የተባለው፡፡

ከዚህ ባለፈም ፖሊስን ጨምሮ ማንኛውንም የፀጥታ ሃይል ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግም እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ጨምሮ አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብም መጣል፣ የሰአት እላፊ ገደብ የማውጣት፣ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴዎችን የማስቆም፣ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ የማድረግ፣ ለተልዕኮ እንቅፋት ይሆናሉ ያላቸውን መግለጫዎች መከልከል፣ ህገ ወጥ በሆነ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች የመያዝና የማቆየት እንደሚችል በተግባር አፈጻጸጸሙ ላይ ተቀምጧልም ብለዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደነገገባቸው አካባቢዎች ላይ ለተልዕኮ ተፈጻሚነት ያግዙኛል ብሎ ሲያምን ሰዎችን በአንድ ቤት፣ ቦታ ወይም አካባቢ እንዲቆዩ የማድረግ ስልጣን እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡

ቤትና አካባቢዎችን ጨምሮ መጓጓዣዎችንም በማንኛውም ጊዜ መበርበርና መፈተሽ እንዲሁም አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን ለተልዕኮ መሳካት ያስችሉኛል ካለ ማስቆም እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

ግብረ ሃይሉ ለተልዕኮ ተፈጻሚነት አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ማድረግ እንደሚችልም ስልጣን የተሰጠው ሲሆን በሂደቱ ተመጣጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

በሃይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.