Fana: At a Speed of Life!

በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን የከፈተውን ዘመቻ ለመመከት በተከፈተው ጦርነት ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል- የሃገር መከላከያ ሰራዊት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን የከፈተውን ዘመቻ ለመመከት በተከፈተው ጦርነት ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን የኢፌዴሪ ሃገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ዛሬ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፥ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ እና ሀገርን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል በተቀመጠው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተከፈተው ጥቃት የሃገር ክህደት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትኛውም አይነት የፖለቲካ ልዩነት በፖለቲካዊ መንገድ ሊፈታ ሲገባ የሰሜን እዝ በራሱ ወገን ጥቃት ተከፍቶበታል ብለዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በተሟላ ብቃት እየመከተ መሆኑን በመግለፅም የተከፈተው ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚቋጭም አስታውቀዋል።

በሰሜን ያለውን ሰራዊት ለማገዝ ከተለያየ የሀገሪቱ አቅጣጫ የሃገር መከላከያ ሰራዊት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስረድተዋል።

ጦርነቱን በመቋጨት ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ሂደት የትግራይ ክልል ህዝብ ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጋር መሆኑን በተግባር አሷይቷልም ነው ያሉት።

ተገዶ ወደ ጦርነት የገባው ልዩ ሃይልም በግልጽ ተቃውሞውን መግለጹን ያነሱት ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ፥ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጦርነቱ የቆሰሉ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትን ለህክምና እያመጣ መሆኑንም አውስተዋል።

በህወሃት ውስጥ ያለው ቡድን ግን ለህዝቡ ደንታ እንደሌለው በከፈተው ጦርነት አረጋግጧል ብለዋል በመግለጫቸው።

አርሶ አደሩ ምርት በሚሰበስብበት ወቅት የተከፈተው ጦርነት የአርሶ አደሩ ልፋት በጥይት እንዲቃጠል የጥፋት ሃይሉ ሆን ብሎ ያቀነባበረው ጥቃት ነውም ብለዋል።

ይህ ቡድን ትግራይን የጦር ቀጠና ሌሎች የሃገሪቱን አካባቢዎች ደግሞ የሽብር ግንባር ለማድረግ ቆርጦ በመነሳቱ ሁሉም ዜጋ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

በአላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.