ስፓርት

የኦሊምፒክ ተሳታፊ  አትሌቶች ከህዳር 1 እስከ 13 ሊዘከሩ ነው

By Meseret Demissu

November 05, 2020

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 26 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሊምፒክ ተሳታፊ ጀግና አትሌቶች ከህዳር 1 እስከ 13  ቀን 2013 ዓ. ም. ድረስ በየተሳተፉባቸው ኦሊምፒኮች ቅደም ተከተል መሠረት ቀን ተሰይሞላቸው እንደሚዘከሩ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላን 60ኛ ዓመት የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ድል ምክንያት በማድረግ  ከሜልቦርን እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ  የተሳተፉ አትሌቶችን ለመዘከር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎም  በኦሊምፒክ መድረክ የተሳተፉ እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በአለም አደባባይ ከፍ አድርገው ያውለበለቡ ጀግኖች አትሌቶችን ለመዘከር የሚያስችል ከህዳር 1 እስከ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ቀን ሰይሞላቸዋል ፡፡

በዚሁ መሠረት  ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የ1956 ሜልበርን ኦሊምፒክ ተሳታፊ ጀግኖች አትሌቶች ቀን ሲሆን በዚያን ጊዜ የተሳተፉ አትሌቶች በሙሉ በፎቷቸው፣ በቪዲዮና በታሪካቸው በሁሉም የህትመት፣ የኤሌክትሮኒክስና ማህበራዊ ሚዲያ ሙሉ ቀን ይዘከራሉ ተብሏል፡፡

ህዳር 2  ደግሞ የ1960 ሮም ኦሊምፒክ ተሳታፊ ጀግኖች አትሌቶች ቀን ሆኖ የተሰየመ ሲሆን ሻምበል አበበ ቢቂላን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶች  በፎቷቸው፣ በቪዲዮ፣ በማብራሪያ ጽሁፎች በሁሉም መገናኛ ዘዴዎች ይዘከራሉም ነው የተባለው፡፡

በዚሁም  መሠረት እስከ ህዳር 13 ቀን ድረስ ማለትም እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ ቀናቶች መሰየማቸውን ከኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።