Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህወሃት ውስጥ ባለ ቡድን ላይ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ ተገቢ መሆኑን ገለፁ

አዲስ አባበ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጅግጅጋ ከተማ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የብልፅግና ፓርቲ፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር፣ የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ፣ ዱቦና ድግኖ ፓርቲ፣ የምዕራብ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና የእኩልነትና የነጻነት ፓርቲዎች ተገኝተዋል።
እነዚህ ፓርቲዎች ውይይቱን ተከትሎ ባለ አራት ነጥብ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን በሀገር መከለከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃት እጅግ አሳፋሪ፣ የሚወገዝና መታለፍ የሌለበት ተግባር ነው ብለዋል።
የፌደራል መንግስትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በፅንፈኛውና ከሃዲው ህወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ተመጣጣኝና ተገቢ እርምጃ እንደሚደግፉ የገለፁ ሲሆን የፌደራል መንግስት የህወሓትን አገዛዝ እንዲያስወግድ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
ፓርቲዎቹ ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በተለይም በሶማሌ ህዝብ ላይ ለ27 ዓመታት በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት ፈፅሟል ነው ያሉት።
የፌደራል መንግስትም ይህንን የፈጸሙ የህወሓት ቡድን አባላት ለህግ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ህብረተሰቡ እንዲረጋጋና ሰላምና ደህንነቱ እንዲጠበቅ ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር ጎን በመቆም ሙሉ ትብብር እንዲያደርግም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ፖርቲዎቹ የሶማሌ ክልል ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ጋር በሰላምና በፍቅር ፣ በአብሮነት ከመኖር ባሻገር ወንድማማችነትና መልካም ጉርብትናን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል ፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.