የሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም 85 በመቶ ይሆናል
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከህዳር 1ቀን 2013 ጀምሮ 85 በመቶ እንደሚሆን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከሲሚንቶ አምራቶችና አከፋፋዮች ጋር በሲሚንቶ ምርት ግብይት እና ስርጭት ሰንሰለት ላይ የሚታዩ ችግሮች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ወቅት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እሼቴ አስፋው እንዳሉት የሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከህዳር 1ቀን 2013 ዓም ጀምሮ አሁን ከደረሰበት 63 በመቶ የማምረት አቅም 85 በመቶ ለማድረስ ስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል፡፡
የብረታብረት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዮሃንስ ድንቃየሁ በበኩላቸው÷ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
አሁንም የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና የማምረት አቅምን በማሳደግ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ድርሻ በተሻለ መጠን ለማስቀጠል ይሰራል ማለታቸውን ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡