የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በእስራኤል ምክትል የደህንነት ሚኒስትር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በእስራኤል ምክትል የደህንነት ሚኒስትር ጋዲ ቫርካን ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የፓርላማና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የኢትዮጵያና እስራኤል የወዳጅነት ኮሚቴ እንደሚቋቋም አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል፡፡
እስራኤል በትምህርት፣ በጤና፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርናው እና በልማት ፕሮጀክቶች ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗንም ነው አፈ-ጉባኤው የጠቀሱት ፡፡
የእስራኤል ምክትል የደህንነት ሚኒስትር ጋዲ ቫርካን በበኩላቸው እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ የደም ትስስር ጠቅሰው፤ የፓርላማ ግንኙነቱን ለማጠናከር የወዳጅነት ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉ የሁለቱን ሃገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝም ገልጸዋል ፡፡
በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ከአንድ ሳምንት በኋላ የአስራኤል መንግስት የሚያደርገው ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡