Fana: At a Speed of Life!

በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም መስፋፋቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጣና ሀይቅ ላይ የተከሠተው የእምቦጭ አረም ከ150 ኪሎ ሜትር ወደ 197 ኪሎ ሜትር መስፋፋቱ ተገለፀ።

ዮም የኢኮኖሚ ልማት ተቋም በጣና ሀይቅ ላይ በተከሠተው የእምቦጭ አረም ዙሪያ ያካሄደውን ጥናታዊ ፅሁፍ በባህር ዳር ከተማ ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቧል።

በውይይት መድረኩ ላይ የጣና ሀይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ልማት ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ፣ የአካባቢ ደንና እንስሳት ልማት ጥበቃ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዶክተር አያሌው ወንዴ የእምቦጭ አረም ከነበረበት ስድስት ወረዳ ወደ ሰባት ወረዳ የተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከ26 ቀበሌ ወደ 27 ቀበሌ የተስፋፋው የእምቦጭ አረም 150 ኪሎ ሜትር የነበረው ይዘቱ አሁን ላይ ወደ 197 ኪሎ ሜትር መድረሱን ገልፀዋል።

ከ4 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የጣና ሀይቅ አካል በእምቦጭ አረም መያዙንም ዶክተር አያሌው አስረድተዋል።

የባህርዳር ዮኒቨርሲቲ መምህር መልካማሪያም ገነት በጣና ሀይቅ ላይ የተከሠተው የእምቦጭ አረም በአካባቢው ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን በጥናታዊ ፅሁፋቸው አመልክተዋል።

በጥናቱም የአሣ ምርት 70 በመቶ፣ የከብት እርባታ 54 በመቶ፣ የሰብል ምርት 25 በመቶ በእምቦጭ አረም ምክንያት ቀንሷል ነው ያሉት።

እንዲሁም የእምቦጭ ቅጠል የበሉ ከብቶች ለስጋ እንደማይሆኑ በጥናቱ ላይ ተመላክቷል፡፡

እንቦጭ አረምን ከጣና ሀይቅ ለማጥፋት የአምስት አመት ስትራቴጂ እቅድ መነደፉን የገለፁት ዶክተር አያሌው እቅዱ፥ ከአምስት አመት በኋላ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

እቅዱን ለማሳካትም 100 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግም ዋና ስራ አስኪያጁ አንስተዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.