Fana: At a Speed of Life!

በሕወኃት ኃይል ላይ የተወሰደው የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ በስኬት እንደተጠናቀቀ ጠ/ሚ ዐቢይ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስግብግቡ ጁንታ የሕወኃት ኃይል ላይ የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ በስኬት መጠናቀቁን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ የአየር ኃይል በወሰደው እርምጃ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የነበሩ ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማውደም መቻሉን ገልፀዋል።

ሮኬቶቹ እስከ 300 ኪሎ ሜትር መወንጨፍ የሚችሉ በመሆናቸው እና በወንጀለኛው ቡድን ሮኬቶቹን የመጠቀም ፍላጎት በመኖሩ በመቐለ እና አካባቢዋ በነበረው የከባድ መሣሪያ ማስቀመጫ ላይ የአየር ኃይሉ እርምጃ እንዲወስድ መደረጉ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ሦስት ዋነኛ አላማዎችን ዘርዝረዋል፡፡
የመጀመሪያው አላማ ጥቃቱን መግታት ነበር ያሉ ሲሆን በዚህም ጥቃት የተሰነዘረባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት ያልነበረባቸው ቢሆኑም ከተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ሙሉ የሎጆስቲክ እና የኃይል አቅርቦት መጠናቀቁን አንስተው የጠላትን ጎዞ ሙሉ ለሙሉ ማስቆም መግታትና ተጨማሪ ጥቃት መሰንዘር ወደማይችልበት ደረጃ አድርሰነዋል ብለዋል፡፡
ሁለተኛው አላማ ደግሞ የመከላከያ ኃይልና የፖሊስ ሰራዊት የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ ይህንን ኃይል የመታደግና ወሳኝ ሃገራዊ ንብረቶችንና ትጥቆች የመታደግ ስራ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
ከዚህ አንጻርም በባድመ ግንባር፣ በጾረና በዛላምበሳ በዋና ዋና ቦታ ተሰልፈው ያሉ የሰራዊት አባላትና ትጥቆቻቸው ከጠላት ፍላጎት ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
እንዲሁም የጠላትን የማድረግ አቅም ማዳካም እንደነበረ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም መሳካቱን ነው የገለጹት፡፡
ይህ ስግብግብ ጁንታ ለህግ እስከሚቀርብ ራስንና ሃገርን ከጥቃት የመከላከል ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ይህን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስወገድ ለትግራይ ሕዝብ፣ ለመከላከያ ሰራዊትና ለፖሊስ ኃይል እፎይታና ሰላም በመስጠት የእርሻ ስራችንን መሰብሰብ የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ይህ ዘመቻ ሲጠናቀቅ ዝርዝር ጉዳዩን ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.