Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ሰፋፊ የአበባ እርሻ መሬት የወሰዱ አልሚዎች ወደ ስራ አልገቡም

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ሰፋፊ የአበባ እርሻ መሬት የወሰዱ አልሚዎች ወደ ስራ እንዳልገቡ ተገለፀ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምልከታ ባደረገባቸው በምዕራብ ሸዋ እና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በዳስ ብቻ የቀሩ ሰፋፊ እርሻዎችን መመልከት ችሏል።

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮችም ለአበባ እርሻ የተወሰደ መሬት ላለፉት ስድስት አመታት ያለ ልማት በመቀመጡ ለችግር ተዳርገናል ይላሉ።

አርሶ አደሮቹ አንድ የህንድ ኩባንያ ከ156 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት በ2003 ዓ.ም መረከቡን እና በወቅቱም ኩባንያው የስራ እድል በመፍጠር ትምህርት ቤትና መሰረተ ልማት እንደሚገነባ ቢገልፅም እስካሁን አንዱንም አለመተግበሩን አንስተዋል።

መሬታቸውን ለ10 አመት ውል ብቻ መስጠታቸውን የሚያነሱት አርሶ አደሮቹ በቃል እንጅ ወረቀት ላይ የሰፈረ ውል በእጃቸው እንዳልያዙም ተናግረዋል፤ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኙ በመጥቀስ።

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮጀክት ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ በላይ ዱፌራ በኩላቸው፥ በህንዱ ኩባንያ የተያዘው ይህ ስፍራ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ በመክሰሩ ስራ ማቋረጡን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮቹ መሬቱን ለ10 አመት ሳይሆን ለ30 አመት ውል መስጠታቸውንም አስረድተዋል።

ድርጅቱ ለስራ ማስኬጃ ከባንክ ከ26 ሚሊየን ብር በላይ መሬቱን አስይዞ በመበደሩ እና ባንኩም ያሉትን ህጋዊ አማራጮች መጠቀም ባለመቻሉ ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ በህግ ሂደት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

ከዚሁ ድርጅት ጋር ትስስር ያለውና በሌላ የንግድ ስም የተመዘገበ ኩባንያ ከ108 ሄክታር በላይ መሬት ለአበባ እርሻ ፕሮጀክት በሆለታ ወስዶ ውጤታማ ባለመሆኑ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሰፋፊ መሬት ለአበባ እርሻ የያዙ ባለሀብቶች የገበያ መውረድ እንደችግር የሚያነሱ ሲሆን ክልሉ በበኩሉ ውጤታማ ባልሆኑትና አጥረው ባስቀመጡት ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.