ለመከላከያ ሚኒስቴርና ለአማራ ክልል ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የሚያውጡ የምግብ ሽቀጦች ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ለመከላከያ ሚኒስቴርና ለአማራ ክልል 7 ሚሊየን 326 ሺህ ብር የሚያውጡ የምግብ ሽቀጦችን የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉሙሩክ ኮሚሽን ድጋፍ አደረጉ።
ርክክቡን የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና ለመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተሩ ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ፈፅመዋል።
ድጋፋን ያስረከቡት አቶ ላቀ አያሌው መንግስት ህግና ስርዓትን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ የገቢዎች ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች ይደግፋሉ ብለዋል።
ህግና ስርዓትን እያስከበሩ ላሉት የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለአማራ ክልል የጸጥታ አካላት የተደረገው ድጋፍ በእነሱው ህግ የማስከበር ስራ የተገኘ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ላቀ ድጋፋ በቂ አለመሆኑን በመግለፅ ዚህ በኋላም ድጋፋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ከዚህ ቀደምም በክልሉ በሚፈጠሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮዊ አደጋዎች በተከሰቱበት ወቅት የተለያዩ ድጋፎችን እንዳደረጉላቸው ገልጸው አሁንም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አያይዘውም በጥፋት ቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ህብረተሰቡን በማይጎዳ መልኩ ብቻ እንደሚደረግ ገልጸው የተሰጠውን ድጋፍም ለኮማንድ ፖስቱ በማሰራጨት ለታለመለት አላማ እንዲውል እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር ኢንዶክትሬሽን ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ በበኩላቸው የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በቀዳሚነተ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን በመግለፅ ጽንፈኛውን ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሀገር መከላከያና የአማራ ክልል የጸጥታ አካላት በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው ብለዋል።
የተበረከተው ድጋፍም 86 ሺህ 820 ሊትር የምግብ ዘይት ፣ 1 ሺ ህ210 ኩንታል ስኳር ፣ 5 ሺህ 500 ኪሎ ግራም ሩዝ ፣ 145 ኩንታል ክክ እንዲሁም 180 ኩንታል ፓስታ ነው ።
በዘመን በየነ