በአሶሳ ለጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሊውል የነበረ ከ14 ሚሊየን ብር በላይና ገጀራዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ለህወሓት የጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያነት ሊውል የነበረ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ የያዙ 59 የባንክ ሂሳብ ደብተሮች፣ ጥሬ ገንዘብ እና ገጀራዎችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
በክልሉ ከህወሓት ተልዕኮ ወስደው ጥፋት ለመፈጸም በማሴር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ከ70 በላይ መድረሱ ተገልጿል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ እንዳስታወቁት፥ የህወሐት ጥፋት ቡድን ክልሉን ብሎም ሃገርን ለማተራመስ የሚያደርገው ሴራ እየከሸፈ ነው።
“ባለፉት ሶስት ቀናት የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ሃይል፣ ጸረ-ሽምቅ፣ ሚሊሻ እና በጎ ፈቃደኞች በተለይም አሶሳ ከተማን ትኩረት በማድረግ በቅንጅት እየሠሩ ይገኛሉ” ብለዋል።
ህብረተሰቡም መረጃ ከመስጠት ባላፈ ተደራጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ መሆኑን ያስረዱት ኮሚሽነሩ፤ ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ መሠረት ለጥፋት ሊውል የነበረ 12 ሚሊየን 800 ሺህ ብር የያዙ 59 የባንክ ሂሳብ ደብተሮች መያዛቸውን ገልጸዋል።
ገንዘቡ በ12 ሰዎች ስም በ14 የተለያዩ ባንኮች በተከፈቱ የቁጠባ ሂሳብ ደብተሮች የተመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል።
ግለሰቦች ስማቸውን እየቀያየሩ የቁጠባ ደብተሩን በማዘጋጀት ገንዘቡን ለጥፋት ለማዋል ሲንቀሳቀሱ እንደተደረሰባቸው ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በሴራው ከተጠረጠረ አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት 1 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በጥሬ መገኘቱን ለኢዜአ አብራርተዋል።
እንዲሁም በከተማው የአንድ ሆቴል ባለቤት በሆነ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ60 በላይ ገጀራ እና ቢላዋ መገኘቱንም ኢዜአ ዘግቧል።