Fana: At a Speed of Life!

በህወሓት ውስጥ ባለው ቡድን ላይ እየተወሰደ የሚገኘውን እርምጃ እንደግፉለን — የትግራይ ተወላጆች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህወሓት ውስጥ ያለ ቡድን የሀገር አለኝታና መከታ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት የትግራይ ተወላጆች አውግዘዋል።
በህወሓት ውስጥ ባለው ቡድን ላይ እየተወሰደ የሚገኘውን እርምጃ እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ተወላጅ አባላት፣ ደጋፊዎችና ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ ወቅት ሃሳባቸውን የሰጡት የትግራይ ተወላጆቹ እንዳሉት፤ የትግራይ ህዝብን የማይወክለው ህወሓት ከተወገደ የትግራይ ህዝብ ሠላሙንና ነጻነቱን ያረጋግጣል፡፡
የህወሓት ውስጥ ያለው ቡድን መሪዎች ተይዘው ለሕግ ቀርበው የህግ የበላይነት ምን እንደሆነ ማወቅ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
በመከላከያ ሰራዊት ላይ ለወሰደው እርምጃና ዕድሜውን ሙሉ ሲሰራ ለነበረው ጥፋት ተግባር የእጁን ማግኘት እንዳለበትም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በዚህ ቡድን ላይ እርምጃ በሚወሰድበት ወቅትም ህዝቡን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ቡድኑ የክፋት መገለጫ መሆኑን ገልጸው፤ እየተወሰደበት ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ፤ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በወንጀለኛው በህወሓት ቡድን ላይ ነው ብለዋል፡፡
የቡድኑ ክህደት አላግባብ ለመበልጸግ ከማሰብና ስልጣንን የሙጥኝ ከማለት የመነጨ እንደሆነ ተናግረዋል።
ወደ ሰላማዊ መስመር እንዲገባ በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ሰላማዊ አማራጭን መጠቀም አለመፈለጉን በተግባር እንዳሳየ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሕገ ወጥ ቡድኑን ለሕግ ማቅረብ ዓላማ ያደረገ እንደሆነም አብራርተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.