Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ የመረዋ – ሶሞዶ – ሰቃ – ሲሞዶ – ሊሙ መንገድ ግንባታን አስጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመረዋ – ሶሞዶ – ሰቃ – ሲሞዶ – ሊሙ መንገድ ግንባታን አስጀመሩ።

የማና፣ ሊሙ ኮሳ እና ሊሙ ሰቃ ወረዳዎችን የሚያቋርጠው መንገድ፥ 94 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው ግንባታው በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።

ለመንገድ ፕሮጀክቱ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚደረግ ሲሆን፥ የቁጥጥር ስራውን ጨምሮ ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል።

ግንባታውን የቻይናው ቱ ሲ ጁ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሲያከናውነው ኋይት ናይት ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ደግሞ የቁጥጥር ስራውን የሚሰራ ይሆናል።

የመንገዱ መገንባት በአካባቢው የሚመረተውን የቡና ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ በተሻለ ፍጥነት ለማቅረብና በስፍራው በግብርና ማቀነባበር ለተሰማሩ ባለሃብቶች ምርታቸውን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።

ከዚህ ባለፈም መንገዱ በጂማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስት አቅራቢያ የሚያልፍ በመሆኑ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ፍሰት ለማሳደግ ያግዛልም ነው የተባለው።

የመንገድ ፕሮጀክቱ በወረዳ 21 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር እንዲሁም በገጠር ከ8 እስከ 10 ሜትር ስፋት ይኖረዋል።

በመንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.