Fana: At a Speed of Life!

በሀገር መከላከያ ላይ የተቃጣው ጥቃት በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የሌለውና የሀገር ክህደት ነው – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር መከላከያ ላይ የተቃጣው ጥቃት በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የሌለውና የሀገር ክህደት መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ።
 
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖርት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዳሉት ÷ ይህ ጥቃት ሳይሆን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ይቅርና ለየትኛውም የሀገራችን ዜጋ የማይገባ፣ በየትኛዉም መመዘኛና መለኪያ ይቅር የማይባል እና የሚወገዝ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ እንዳሉት÷ ይህ የህውሃት የጥፋት ቡድን ባለፉት ዘመናት ሀገሪቱን በመራበት ዓመታትም ሆነ አሁን ከስልጣን ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ፣ በርካቶቸን እያፈናቀለ እና አሰቃቂ ኢሰብአዊ ድርጊት እየፈፀመ ኖሯል ነው ያሉት።
 
ይህ ደግሞ ተግባሩና ንግግሩ ለየቅል መሆኑን ተናግረው አሁን በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የፈፀመው ግን ከሁሉም የከፋና የሀገር ክህደት እንደሆነ አስረድተዋል።
 
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው ÷ ይህ ቡድን ሀገሪቱ በርካታ አንገብጋቢ፣ ፈታኝ እና ቀጣይ እጣ ፋንታዋን መወሰን የሚያስችሉ ጉዳዮችን እየፈፀመች ባለበት ወቅት ለበርካታ ዘመናት ለአካባቢው ህዝብ ዋስትና እና መከታ በሆነው መከላከያ ላይ ያደረሰው በእርግጥም ከቃል በላይ የቡድኑን አሳፋሪነትና ውርደት በተግባር ያየንበት ነው ብለዋል።
 
እንደ ፓርቲ አመራሮቹ ገለጻ ይህ የትህነግ የጥፋት ቡድን በዜጎችና በኢትዮጵያ ላይ ክህደትና ጥፋትን ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል ያሉ ሲሆን ÷አሁን በሀገሪቱ የጀርባ እጥንትና የምንጊዜም መከታ በሆነው መከላከያ ላይ ያደረሰው ትንኮሳ ቡድኑ መቼም ቢሆን ከስህተቱ የማይማርና ለሃገሪቱና ለዜጎቿ ውድቀት የማይተኛ መሆኑን ያሳየበትና ያረጋገጠበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
በመሆኑም መከላከያውም ተገዶ የገባበትንና ጦርነትና እራሱን ለመከላከል እየወሰደ ያለዉን እርምጃ የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ይህን የጀመረውን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ባጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባው አሳስበዋል።
 
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ይህ በሀገርና በወገን ላይ የተቃጣውን ደርጊት ከመመከት ባሻገር ይሄዉ የጥፋት ቡድን ያሰማራቸውን ተላላኪዎች የመከታተልና ለህግ የማቅረብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።
 
በሙሀመድ አሊ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.