Fana: At a Speed of Life!

ህወሓትን መደገፍ ወንጀል ነው – አገው ብሔራዊ ሸንጎ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመውን የህወሓት ቡድን መደገፍ ወንጀል ነው ሲል የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ኮነነ።

መንግስት በህወሓት ላይ የጀመረውን ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲያጠናክር፣ ሕወሓትም በድርጊቱ ተጸጽቶ ምህረት ሊጠይቅ እንደሚገባው ገልጿል።

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ አመራሮች የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት እጅጉን እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው ቡድኑ ከሰሞኑ ሃገርን በሚጠብቀውና የክልሉን መንግስት አምኖ በተቀመጠው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ፈፅሞ ከወታደራዊ ህግ ያፈነገጠ፣ ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ድርጊት ብለውታል።

ህወሓት ትግል ላይ በነበረበትም ሰዓት ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰሰቡ ለነጻነት የሚታገሉ የኢህአፓ ታጋዮችን በተኙበት በጅምላ እንደረሸናቸው አስታውሰዋል።

አሁንም ህወሓት መንግስት ሆኖ በሚመራው ክልል ሃገር ዳር ድንበር የሚከላከል ሰራዊት መንግስትን አምኖ በተቀመጠ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም በኢትዮጵያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ክህደት መፈጸሙን አውስተዋል።

የድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ መስፍን ህወሓት የፈጸመው ድርጊት ፓርቲውን እንዳሳዘነው ነው የገለጹት፡፡

መንግስት ሕግ ለማስከበር የወሰናቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ጊዜያዊ መንግስት የማቋቋምና የሕግ ማስከበር እርምጃዎች የሚደገፉ መሆናቸውን ገልጸው ÷ህግ ማስከበር ስራውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በአንድ አገር ሁለት መንግስት አይኖርም ያሉት አመራሮቹ÷ የዜጎችን ሰላም ደህንነት ለመጠበቅ ብሎም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዳይፈርስ ለመከላከል ህግ ማስከበር የመንግስት ግዴታ እንደሆነ አብራርተዋል።

መንግስት ሕግ በማስከበር ሂደትም ንጹሃን እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ማድረግና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ አለበትም ነው ያሉት።

የትግራይ ሕዝብም ስጋት ሳይገባው ከኢትዮጵያውያን ጎን ሊቆም ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.