Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት አጥፊ ቡድን ዛሬም በማጭበርበር ተግባሩ እርስ በእርሱ በተጣረሱ የእያሸነፍን ነውና የእንደራደር ሀሳቦችን እየሰነዘረ ነው- አቶ ነቢዩ ስሁልሚካኤል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት አጥፊ ቡድን ዛሬም የማጭበርበር ተግባሩን እርስ በእርሱ በተጣረሱ የእያሸነፍን ነውና የእንደራደር ሀሳቦችን እየሰነዘረ መሆኑን የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል ገለፁ።
አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የህወሓት አጥፊ ቡድን በህዝብ ግፊት መቐለን መሸሸጊያ ከማድረግ ባለፈ በአምባ ገነናዊ አካሄድ ለውጥ ፈላጊዎችን ጭምር አፍኖ ትግራይን የአማራጭ ሀሳብ አልባና ጸረ ለውጥ አስመስሎ ለመሳል ጥረት አድርጓል ይላሉ።
ምንም እንኳን የህወሓት አጥፊ ቡድን ሀገር እስከማፍረስ የሚደርስ አካሄድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንደቤተሰብ በሚተያየውና የሀገር መከታ በሆነው መከላከያ ሀይል ላይ ጥቃት ያደርሳል የሚል ግምት እንዳልነበረ ያነሳሉ።
ድርጊቱን የትግራይ ህዝብን ያሳዘነ ህዝብን ያስቆጣ ነው ያሉ ሲሆን፥ ህብረተሰቡ ባገኘው አጋጣሚ ከመከላከያ ጎን መሆኑን ያሳየበት አልፎም የክልሉ ልዩ ሀይል ጭምር አካሄዱ ትክክል አይደለም ብለው የሸሹበት መሆኑንም አውስተዋል።
በፖለቲካ ማሸነፍ እንደማይችል ሲያረጋግጥ ሌላኛውን የጥፋት አቅጣጫ የተከተለው ይህ ቡድን ጦርነቱ እንደማያዋጣው እያወቀ ወደዚህ ተግባር የገባው ውጥረት በመፍጠር ወደ ድርድር ገብቶ እውቅናን ለማግኘት እንደሆነም አንስተዋል።
ሰሞነኛው የተጣረሱ የእንደራደርና የእያሸነፍን ነው ፕሮፖጋንዳም የዚህ ማሳያ እንደሆነም ነው የሚያነሱት፡፡
የህወሓት አጥፊ ቡድን ችግሮችን በድርድር የመፍታት ልቦና ቢኖረው በተደጋጋሚ ከወራት በፊት ሰፋፊ እድሎች ነበሩት።
አላማው ሌላ በመሆኑ የሰላም ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ በየእለቱ ህገ መንግስታዊ ጥሰትና በጦር አውርድ ፖሮፓጋንዳ ተጠምዶ መዋልን መርጧል ይላሉ አቶ ነብዩ።
የፌደራል መንግስት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የህወሓትን የጥፋት አካሄድ በትግእስት ቢያልፈውም አሁን የማይነካውን ነክቷል የማይደፈረውን ደፍሯል፤ ለሁሉም ነገር ቀይ መስመር አለውና አሁን አንድና አንድ አማራጩ የአጥፊውን ቡድን ለህግ ማቅረብ ነው ብለዋል ሀላፊው።
የአንድ ነገር መጥፊያው መነሻውና ሂደቱ አመላካች ነው የህወሓት እሳቤውም ትክክል ያልሆነ በመሆኑ መጥፊያው ተፋጥኗል ሲሉም ተናግረዋል።
ስለዚህም በህወሓት ውስጥም ያሉ ለውጥ ፈላጊዎችም ሆነ የክልሉ ጸጥታ ሀይል የነበረበትን አፈና ከውስጥ በመግፋት የአጥፊ ቡድኑን እድሜ እንዲያጥር ሊያደርግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቀጥሎ ክልሉ በተረጋጋና በተደራጀ መንገድ ወደ ልማትና ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ራሱን ማዘጋጀት አለበት ብለዋል አቶ ነብዩ።
ለዚህም የሚሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ራሱን የቻለ ጊዜያዊ መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
በሀይለኢየሱስ ስዩም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.