Fana: At a Speed of Life!

ከሽራሮ እስከ ዛላንበሳ ድረስ ያሉት የሰሜን እዝ የጦር ክፍሎች በአሁኑ ሰዓት በጥሩ የዝግጁነት አቋም ላይ ይገኛሉ- ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሽራሮ እስከ ዛላንበሳ ድረስ ያሉትን የሰሜን እዝ የጦር ክፍሎች በአሁኑ ሰዓት በጥሩ የዝግጁነት አቋም ላይ እንደሚገኙ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ገለፁ።
ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በዛሬው እለት መግለጫ መስጠታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመግለጫቸውም ከሽራሮ እስከ ዛላንበሳ ድረስ ያሉትን የሰሜን እዝ የጦር ክፍሎች በአካል አግኝተው መመለሳቸውን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሁሉም ከሽራሮ እስከ ዛላንበሳ ድረስ ያሉት የሰሜን እዝ የጦር ክፍሎች በጥሩ የዝግጁነት አቋም ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
በመግለጫቸው በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ የህወሓት ቅጥረኞች ሠራዊቱን ከውስጥ የማፍረስ፣ ሠራዊቱን መውጋት እና ማዘናጊያ የሽምግልና ስራ የመስራት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ሁሉንም መፈጸማቸውንም አውስተዋል፡፡
ሠራዊቱን ከውስጥ ለማፍረስ የሰሜን ዕዝን የሬዲዮ መገናኛ አዲስ አበባ በሚገኘው የመገናኛ ሀላፊ አማካኝነት ወደነሱ ማዞራቸውን ያነሱት ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ፥ በዚህም መከላከያ እና ጦሩ እርስ በርሱ እንዳይገናኝ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም የሠራዊቱን የወር ደመወዝ እና ቀለቡን በመውሰድ አዛዦችን ማፈናቸውንም አንስተዋል፡፡
ሰራዊቱም ይህ ሁሉ ተፈጽሞበት በጀግንነት መዋጋቱንም ነው ያወሱት፡፡
በወቅቱ በተደረገው ውጊያ ከትግራይ ልዩ ሃይል በተጨማሪም በዛላንበሳ፣ በሽራሮ፣ በራማ ፣ በፆረና እና በሌሎች ቦታዎች የኦነግ ሸኔ አባላት ባንዲራቸውን ይዘው አብረው ተዋግተዋልም ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡
አሁን ላይም የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጀኔራል አበባው ታደሰ በስፍራው በመገኘት ሠራዊቱን እየመሩት እንደሚገኙም ነው የገለጹት፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.