በቁጥጥር ስር የዋሉ የህወሓት ታጣቂዎች ልዩ ኃይሉና ወጣቱ የጥፋት ቡድኑ እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ ከመሆን እንዲቆጠቡ አስገነዘቡ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ልዩ ኃይሉና ወጣቱ የጥፋት ቡድኑ እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆን የለባቸውም ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ የጽንፈኛው ህወሓት ቡድን ታጣቂዎች ገለጹ።
ከአንድ ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ቡድን የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የሃገር መከላከያ ሠራዊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተሰጠው ሃገርን የማዳን ተልዕኮ ሕግ ለማስከበር የዘመቻ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የሠራዊቱ 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የህወሓትን ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር አውሏል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ታጣቂዎች የትግራይ ልዩ ኃይልን የተቀላቀሉት ኑሯቸውን አሸንፈው ለማደግ እንጂ ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ለመዋጋት አለመሆኑን ገልጸዋል።
ኑሮን ለማሸነፍ በሚል ወደ ልዩ ኃይሉ ቢገቡም የህወሓት የጥፋት ቡድን እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ ከመሆን ውጪ ያገኙት ነገር አለመኖሩን ነው የተናገሩት።
ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ጋር መጋጨት ማለት ከኢትዮጵያ ጋር መጋጨት መሆኑንም ገልጸዋል።
የትግራይ ልዩ ኃይል እና ወጣትም የህወሓት የጥፋት ቡድን ሰላባ እንዳይሆኑ ከሃገር መከላከያ ሠራዊቱ ጎን መቆም እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በሃገር መከላከያ ሠራዊቱ የደረሰባቸው ምንም አይነት ችግር እንደሌለና በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
የሃገር መከላከያ ሠራዊት እያከናወነ ባለው ዘመቻ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።