በአዲስ አበባ በበቀን 600 ሺህ ሊትር ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ በቀን 600 ሺህ ሊትር ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ ተጀመረ።
በሆራይዘን ፕላንቴሽን ባለቤትነት የሚተዳደረው የሸገር የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ፥ በሜድሮክ ኢትዮጵያ አማካኝነት ቦሌ ክፍለ ከተማ የተባበሩት አደባባይ አካባቢ የሚገነባ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሜድሮክ ኢትዮጵያ በዘይት ፋብሪካ ግንባታ ለመጀመር መነሳቱ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ለግንባታው አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ጠቅሰው፥ ባለሀብቶች እንደ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ስራ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የፋብሪካው መገንባት ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው የዘይት ምርት በ25 በመቶ እንዲቀንስ ያደርጋል ነው የተባለው።
ፋብሪካው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ መጠን ያቀርባል ተብሏል።
የፋብሪካው ግንባታ በአንድ አመት ተኩል ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።