Fana: At a Speed of Life!

ከህወሓት ተልዕኮ ወስደው በሲዳማ ክልል ጥፋት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከህወሓት የጥፋት ቡድን ተልዕኮ ወስደው በሲዳማ ክልል የህዝቡን ሰላም ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ የህወሓትን የጥፋት ተልዕኮ ለማምከን  በርዕሰ መስተዳደሩ የሚመራ ዐቢይ ኮማንድ ፖስት ተደራጀቶ እየሰራ መሆኑን ተናገረዋል።

ከክልሉ የፀጥታ አካላት፣ ሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት በአባልነት ያቀፈው ኮማንድ ፖስቱ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የተቀናጀ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከህወሓት የጥፋት ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው በክልሉ በተለይም በሀዋሳ ከተማ ላይ ጥፋቶችን ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታወቀዋል።

ከነዚህ ውስጥ አምስቱ የኦነግ ሸኔ አባላት እንደሆኑ ጠቁመው፤ ሌሎቹ በቀጥታ ከህወሓት ቡድን ተልዕኮ ወስደው ወደ ክልሉ የገቡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል በተለይ በሀዋሳ ከተማ በሆቴል ውስጥ ተሸሽገው የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ የሚያሰማሯቸውን ወጣቶች ሲመለምሉ የነበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጥፋት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ከተያዙት ግለሰቦች በተጨማሪም ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ መያዙን ገልጸው፤ ከ36 ሺህ ብር በላይ ሀሰተኛ የብር ኖቶች፣ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ82 በርሜል በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል።

“የክልሉ መንግስት በቀጣይም የህብረተሰቡ ሥጋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ይገኛል” ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ከዛሬ ጀምሮ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪና ባለ ሁለት እግር ሞተር ተሽከርካሪ በክልሉ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ እገዳ መጣሉን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.