ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ በንቃትና በተደራጀ መንገድ አካባቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ በንቃትና በተደራጀ መንገድ አካባቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የህወሓት ጁንታ ፀሐይ እየጠለቀች መሆኑን ጠቅሰው፥ “ይሄንን መርዶ ጁንታው በቁሙ ተረድቶታል” ብለዋል።
ጁንታው አሁን የሚይዘውን የሚጨብጠውን የሚያጣበት ጊዜ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “በጣዕር መንፈስ በየቦታው የመጨረሻውን የጥፋት ድግስ ይደግስ ይሆናልም” ነው ያሉት።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ወገኖች በየአካባቢው ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይደርስባቸው ሁሉም የወንድሞቹ ጠባቂ እንዲሆንም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ጠላት ስግብግቡ ጁንታ መሆኑን በመጥቀስም የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው ሕዝብ በጁንታው መከራ ያየ ሕዝብ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጁንታው ለፍርድ እንዲቀርብ የትግራይም ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር አብሮ እየተዋጋ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ህዝቡም አካባቢዬን እጠብቃለሁ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የመከራ ቀንበር እሰብራለሁ፤ ጁንታውን ለፍርድ አቀርባለሁን ቃል ኪዳኑ ሊያደርግ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።