Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የእብድ ውሻ በሽታ እየተበራከተ ቢመጣም የበሽታው መከላከያ መድሃኒት በጤና ተቋማት እየቀረበ አይደለም ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የእብድ ውሻ በሽታ እየተበራከተ ቢመጣም የበሽታው መከላከያ መድሃኒት በጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ እየቀረበ አይደለም ተባለ።

የእብድ ውሻ በሽታ ከታከሙት ሙሉ በሙሉ የሚድን ሲሆን ከተላላፊ በሽታዎች በገዳይነቱም ይጠቀሳል።

በሽታው 90 በመቶ ከውሻ እና 10 በመቶ ደግሞ የውሻ ዝርያ ካላቸው እንሰሳት እንደሚመጣም በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ባለቤት የሌላቸው ውሻዎች በብዛት እየተሰተዋሉ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።

በተለይ በከተማዋ ለመልሶ ማልማት በተለቀቁ ቦታዎች ላይ ባለቤት የሌላቸው ውሻዎች መበራከታቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ነው የገለጹት።

የሚመለከተው አካልም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

በሀገሪቱ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብቻ ይሰጥ የነበረው የእብድ ወሻ በሽታ ህክምና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እና በአዲስ አበባ 5 ክፍለ ከተሞች እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ሆኖም ፋና ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የኢትዮዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፤ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ህዳሴ ጤና ጣቢያ እንዲሁም ንፋስ ስልክ ጤና ጣቢያ ወረዳ 12 ህክምና መስጫዎች የእብድ ወሻ በሽታ መድሀኒት ባለመኖሩ ህክምናውን ለመስጠት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቡድን አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸው ግርማ በአሁኑ ወቅት በበሽታው ተይዞ የሚመጣው ሰው እና የመድሀኒት አቅርቦቱ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የኢትዩጵያ የመድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በበኩሉ ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ከሚያቀረባቸው መድሀኒቶች ዝርዝር ውስጥ የእብድ ውሻ መድሀኒት ከአንድ ዓመት በላይ አልተካተተም ብሏል።

መድሃኒቱ ጤና ጣቢያዎቹ በሚልኩት የመድሃኒት ዝርዝር ውስጥ ቢያካትቱት ማቅረብ ይቻል እንደነበር የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ወይዘሮ አድና በርሄ ገልፀዋል።

በሲሳይ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.