Fana: At a Speed of Life!

ከበባ ውስጥ ገብቶ ለአምስት ቀናት ምግብና ውሃ ተከልክሎ የነበረው የሰሜን ዕዝ ጦር ከከበባ በመውጣት መልሶ እያጠቃ ነው– ጀኔራል ብርሃኑ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህወሃት ውስጥ ባለ የጥፋት ቡድን ከበባ ውስጥ ገብቶ ለአምስት ቀናት ምግብና ውሃ ተከልክሎ የነበረው የሰሜን ዕዝ ጦር ከከበባ በመውጣት ራሱን መልሶ በማደራጀት እያጠቃ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደፊት በመገስገስ ላይ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
በጥፋት ቡድኑ ከበባ ውስጥ ገብቶ የነበረው 7ኛ ሜካናይዝድ፣ 8ኛ ሜካናይዝድ፣ 23ኛ ክፍለ ጦር፣ 11ኛ ክፍለ ጦር፣ 31ኛ ክፍለ ጦር፣ 20ኛ ክፍለ ጦር፣ 4ኛ ሜካናይዝድ፣ 5ኛ ሜካናይዝድ በሙሉ የሰሜን እዝ ሰራዊት እንደነበረ ለኢዜአ ገልጸዋል።
“ይህ ሰራዊት ለአራትና አምስት ቀናት ምግብና ውሃ ተከልክሎ፣ ራሱን በውሃ ጥም ውስጥ ሆኖ በፅናት የተከላከለ ጀግናና የመከላከያ ሰራዊታችን ሞዴል ሆኖ በመገኘቱ በራሴና በኢትዮዽያ ህዝብ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ” ብለዋል።
የሰራዊቱ ጀግንነትም ሲዘከር የሚኖር ገድል መሆኑን የገለፁት ጄኔራሉ “እውነተኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰራዊት መሆናቸውን በተጨባጭ ስላስመሰከሩም ከፍተኛ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ” ነው ያሉት።
ሰራዊቱን ከከበባ ለማላቀቅ ከምስራቅ፣ ከደቡብና ከምዕራብ ፈጥነው በመድረስ የሰሜን እዝን ለመታደግ ለቻሉት የሰራዊቱ አመራርና አባላት የ“እንኳን ደስ ያላችሁ” መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከዚህ በኋላ ቀሪው የሰራዊቱ ተልዕኮ እስካሁን ከተፈጸመው ተግባር አንጻር አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት ጀኔራል ብርሃኑ፤ ሰራዊቱ ይህንን በመረዳት ቀሪውን ተልዕኮ በአጭር ጊዜ እንደሚወጣ ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል።
ሰራዊቱ ከከበባ በመውጣትና ራሱን መልሶ በማደራጀት ባለፉት ሁለትና ሶስት ቀናት ከዳንሻ ጀምሮ ሁመራ በሚገኘው ትርካን አየር ማረፊያ እንዲሁም ባዕከርን በማጥቃትና በመቆጣጠር 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦርን ከከበባ ማላቀቁን ተናግረዋል።
ከከበባ ከተላቀቀው 5ኛ ሜካናይዝድ ጋር በመሆንም ሁመራን ነፃ በማውጣት ሉግዲ፣ ማይካድራንና በረከትን ነፃ እንዳወጣ አመልክተዋል።
ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ከሁመራ 60 ኪሎሜትር ወደ ምስራቅ ኢድሪስ በሚባል ቦታ ላይ የጥፋት ቡድኑን እየደመሰሰ እንደሚገኝ ያመለከቱት ጀኔራል ብርሃኑ፤ “ሰራዊቱ በተፈፀመበት ኢሰብዓዊ ድርጊት በመበሳጨቱ በከፍተኛ ወኔ፣ ጀግንነትና ተነሳሽነትም ሁሉንም ነገር ወደነበረበት ለመመለስና ከሃዲውን ቡድን በህግ ፊት ቀርቦ እንዲቀጣ ለማድረግ እየሰራ ነው” ብለዋል።
ሰራዊቱ የትግራይን ህዝብና የትግራይን የፀጥታ ሃይል ጭምር ነፃ ለማውጣት ግስጋሴውን ወደ ሽሬ መቀጠሉን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጠቁመዋል።
“ህገወጡ ጁንታ ህዝቡና የፀጥታ ሀይሉን እንደ ምሽግ ስለተጠቀመ፣ ህዝቡንና የፀጥታ ሀይሉን ከዚሁ ወንጀለኛ ቡድን በመነጠልና እሱኑ ኢላማ ያደረገ እንቅስቃሴ እየተካሄደም ይገኛል” ያሉት ጀኔራል ብርሃኑ፤ ህግ የማስከበሩን ስራ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ጁንታውን ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡ እንዳይጎዳ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.