የሀገር ውስጥ ዜና

በህወሓት ውስጥ ያለው ወንጀለኛ ቡድን ፍርሃትን ለመንዛትና የሽብር ጥቃትን ለማድረስ አስፈፃሚ መረብ ማቋቋሙ ተገለፀ

By Tibebu Kebede

November 12, 2020

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህወሓት ውስጥ ያለው ወንጀለኛ ቡድን በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ፍርሃትን ለመንዛት እና የሽብር ጥቃትን ለማድረስ አስፈፃሚ መረብ ማቋቋሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አሳወቀ፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚያካሂደውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የሕግ ማስከበር ኦፕሬሽን መረጃ ማጣሪያ እንዳስታወቀው ግጭቶችን ለማነሳሳት እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶችን ለማካሄድ ተልዕኮ ከሕወሃት ወስደው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከተለያዩ የኑሮ ሁኔታ እና የሙያ መስክ የተውጣጡ፣ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች ናቸው ብሏል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ጠቅላላ ቁጥር ወደ 150 አካባቢ ሲሆን ከነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል ጥቂቶቹ የሚደቅኑት የፀጥታ ስጋትን አነስተኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዋስ ተለቀዋል፡፡

አንዳንድ አለም አቀፍ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በተሳሳተ መንገድ የተጠርጣሪዎቹን ቁጥር ያልተረጋገጠ እና የተጋነነ መረጃ እያሰራጩ የሚገኙ ሲሆን የሕግ አስከባሪያችን አሠራር ደንብን የተከተለ እንጂ እንደሚወራው በማንነት ላይ ተመስርቶ ግለሰቦችን የሚያጠቃ አይደለም ብሏል፡፡

ሁሉም ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ተዋንያን በሕወሃት የጥፋት ቡድን እየተፈፀመ ያለውን የውሸት የመረጃ ዘመቻ ልብ እንዲሉ ጥሪ እናቀርባለንም ብሏል።