Fana: At a Speed of Life!

በአቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በቻይና የሥራ ጉብኝት አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከታህሳስ 13  ጀምሮ ለአራት ቀናት በቻይና የስራ ጉብኝት አደረገ።

የልኡካን ቡድኑ በቆይታው ከቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ (ICBC)፣ ከቻይና የወጭ ንግድና ብድር ዋስትና ኮርፖሬሽን (SINOSURE)፣ ከቻይና ብሄራዊ ልማትና ሪፎርም ኮሚሽን (NDRC)፣ ከቻይና ንግድ ሚኒስቴር (MOFCOM)፣ ከቻይና ወጭና ገቢ ባንክ (EXIM Bank)፣ ከቻይና ልማት ባንክ (CDB) እና ቻይና- አፍሪካ ልማት ፈንድ (CADFund) ከፍተኛ የመንግስት ሃላዎች ጋር ተገናኝቶ በሁለቱ አገራት የልማት ትብብር ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

የልዑክ ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ለውጥ ለቻይና ባለስልጣናትና ለተቋማቱ ኃላፊዎች ያስረዳ ሲሆን፥ በዚህ ታሪካዊና ወሳኝ ወቅት የቻይና መንግስት ለውጡን በተጠናከረ መንገድ እንዲደግፍ ጠይቋል።

ሁለቱ አገራት በቻይና አፍሪካ ፎረም (FOCAC)፣ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ፣ በሁለቱ አገራት መካከል በተመሰረተው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጅያዊ ትብብር ስምምነት እና በውጤታማ የአቅም ግንባራ ትብብር ማዕቀፎች በመመስረት በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚኖረው የልማትና የኢንቨስትመንት ትብብር ከምንጊዜውም በተሻለ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሁለቱ ወገኖች ተስማምተዋል።

አቶ አህመድ ሺዴ ከላይ ከተጠቀሱት ተቋማት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ ያሉና ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ ከሚገኙ የመንግስትና የግል ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሆነው በሚጠናቀቁበት ሁኔታ ላይ መግባባት ላይ መደረሱንና  ባለሃብቶቹ የመንግስትን የኢኮኖሚ ሪፎርም ተከትሎ ወደ ግሉ ይዞታ በሚተላለፉ ፕሮጀክቶች ላይም እንደሚሳተፉ መገለፁን ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.