Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ በተጓደለበት አንድ አባል ላይ የቀረቡትን አዲስ የምርጫ ቦርድ አባል ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 3፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተጓደለበት አንድ አባል ላይ የቀረቡትን አዲስ የምርጫ ቦርድ አባል ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡

አዲሱ የምርጫ ቦርድ አባል አቶ ፍቅረ ገብረህይወት ሲሆኑ የስራ ልምዳቸውም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት ያገለገሉና በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡

አዲሱ የምርጫ ቦርድ አባል አቶ ፍቅረ ገብረህይወት በምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

ሌላ ምክር ቤቱ የተመለከተው የኤክሳይዝ ታክስን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ  በተመለከተ የገቢ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አጽድቋል፡፡

የረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ከነሃሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የጸና እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ምርቶችን የሚያመርቱ ወይም ወደ ሃገር የሚያስገቡ ግብር ከፋዮች ከሚመለከተው ባለስልጣን ፍቃድ ለማውጣት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በተሰጠው የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ አዳጋች በመሆኑ ማሻሻያው አስፈልጓል የተባለው፡፡

በተጨማሪም በመሸጋገሪያ ድንጋጌ የተሰጠው የስድስት ወራት ጊዜ ካበቃ በኋላ ፍቃድ ሳይኖራቸው የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ምርቶች የሚያመርቱ ወይም ወደ ሃገር ውስጥ የሚያስገቡ ግብር ከፋዮች ተፈጻሚ የማያደርጉ ከሆነ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣቸው ይሆናል ተብሏል፡፡

በመሆኑም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የመሸጋገሪያ ጊዜ እንዲራዘም በማስፈለጉ በአዋጁ የተቀመጠው የመሸጋገሪያ ጊዜ ከነሃሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ታሳቢና ተፈጻሚ እንዲሆን ምክር ቤቱ ማሻሻያውን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

 

 

በሃይለኢየሱስ ስዩም

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.