ጠንካራ የምርምር ተቋሞችንና ቤተ ሙከራዎችን መገንባት ትልቁ ትኩረታችን ነው-ኢ/ር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ ፣ህዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢፌዲሪ ማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጠንካራ የምርምር ተቋሞችንና ቤተ ሙከራዎችን መገንባት ትልቁ ትኩረታችን ሲሉ ገለጹ።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ÷ከየትኛውም ሀገር እድገት ጀርባ ጠንካራ የምርምር ተቋማትና ቤተ-ሙከራዎች አሉ ብለዋል።
እኛም ስለማደግና ስለመበልፀግ ስናስብ ጠንካራ የምርምር ተቋሞችንና ቤተ ሙከራዎችን መገንባት ትልቁ ትኩረታችን ነው።
ይህም በተለይ ለሃገር በቀል ኢኮኖሚ ፍቱን መድሃኒት ይሆናልም ነው ያሉት።
ሚኒስትሩ በዛሬው እለትም የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላብራቶሪን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ጋር ያለበትን ቁመና መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
የማዕድን ቤተሙከራ እና የምርምር ተቋሙ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም አሁን ያለበት ደረጃ እድሜውንና ልምዱን የሚመጥን አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
የዚህ ተቋም በተገቢው መልኩ አለማደግና ትኩረት አለማግኘት ሀገራችንን በየአመቱ በሚሊየኖች የሚገመት ዶላር ለናሙና ምርመራ ወርቅን ለማጣራት እንድታወጣ እያደረጋት ይገኛልም ብለዋል።
ይህ የረጅም አመት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት ተቋም በሚገባው መጠን ማደግና ማዘመን፣ ከባለድርሻዎች እና ከማዕድን አምራቾች ጋር በጋራ በመሥራት ወደ ውጪ የምላኩ ጥሬ ሀብቶች የዕሴትና የግብይት ሰንሰለት እናበጅላቸዋለንም ነው ያሉት።
በቀጣይም ተቋሙን በሰው ሀይል የምናደራጅበት ያለውን አቅም የምናሳድግበት እንዲሁም በዘመናዊ መሳሪያዎች የምናሟላበት ጊዜም ነው ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የናሙና ምርመራ እና የማቅለጫ ከባለሃብቶች ጋር በሽርክና ለማደራጀትና ለመሥራት በዘርፉ የተሰማሩ ሀገር በቀል ኩባንያዎችና ዓለም ኣቀፍ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
ይህ ላብራቶሪ ተደራጅቶ ሲጠናቀቅ ለናሙና ምርመራ ውጪ የሚላከውን ጥሬ ሃብት ሃገር ውስጥ በማስቀረት የውጪ ምንዛሪ ወጪያችንን የሚያስቀር እና ለማእድን ዘርፉ እድገት ደግሞ መንገድ ጠራጊ ይሆናል ብለዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።