ለህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ስኬት የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደወትሮው በስኬት እንዲጠናቀቅ የዝግጅት
ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብያት ጌታቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እ.ኤ.አ ከየካቲት 6 እሰከ 10 ባለው ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል።
ለጉባኤው ዝግጅትም የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኮሚቴው ከጸጥታ፣ ትራፊክ ፍሰት፣ ከሆቴሎች መስተንግዶና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች መካሄድ ጀምረዋል።
እንደ አቶ ነብያት ገለጻ፤ በአዲሱ የፈረንጆች አመት የመጀመሪያ ወቅት ላይ የሚካሄደው ጉባኤ ዋና ትኩረት የሰላም ጉዳይ ነው።
በአጀንዳ 2063 እንደተቀመጠው የአፍሪካ አህጉር የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነም አመልክተዋል።
በዚሁ መሰረት አፍሪካ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተኩስ ድምጽ የማይሰማበት እንዲሆን ለማስቻል የህብረቱ አባል አገሮች እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ጉባኤው በአፍሪካ ህብረት ከተቀመጡ አጀንዳዎች ጋር ተያይዞ ሰላም ለማስፈን የሚያጋጥሙ ችግሮችንና መፍትሄዎችን በጥልቀት የሚመረምርበት መድረክ መሆኑንም አቶ ነብያት ተናግረዋል።
በቀጠናው ሰላም ለማስፈን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በኖቤል ሽልማት ዕውቅና የተሰጣቸው በመሆኑም ጉባኤው ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ስራዎችን የምታሳይበት መድረክ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ህብረት የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በስፋት እያከናወነ ሲሆን የለውጡ ዋነኛ ትኩረት ተቋሙ ኃላፊነቱን መወጣት የሚችልበት መንገድና የተጠያቂነትን ባህል የማዳበር ስራዎች ናቸው።
የአህጉሩ ህዝቦችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚቻልባቸው መንገዶች
ላይም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተው
ጊዜ ጀምሮ የህብረቱን ጉባኤ ስታካሂድ ለ57ኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።