የሐረማያ እና የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ህዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሐረማያ እና የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት ገልፀዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ ለጀመረው ህግ የማስከበር ሂደት የአምስት ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ ÷ የሃገር መከላከያ ሠራዊት እያደረገ ላለው ጥረት ድጋፍ የሚሆን የአምስት ሚሊየን ብር መለገሱን አስታውቀው ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገርም ደም በመለገስ አጋርነታቸውን እንደሚያሣዩ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በጦርነቱ ሊደርስ የሚችለውን ሰብአዊ ጉዳት በመገንዘብ ከወር ደሞዛቸው ላይ አስተዋፅኦ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች “ደሜ ለሃገሬ መከላከያ ሠራዊት” በሚል የደም ልገሳ አካሂደዋል።
በተያያዘ ዜናም የአርሲ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ የሚመመክር መድረክ አካሂደዋል።
የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው ጥቃትና ክህደት የቡድኑን አውሬያዊ ፀባይ ያጋለጠ ነው ብለዋል።
በመድረኩም “የህወሓት ክህደትና ድብቅ አላማ” በሚል ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ÷በሰነዱም የፅንፈኛው ቡድን ከምስረታ እስከ አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ የነበረው ቦታና ሸፍጥ ተዳሷል።
የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አልዬ ህወሓት በሀገር ፖለቲካ ላይ በስልታዊ የተንኮል ቀመር ራሱንና እሱ ያደራጃቸውን ቡድኖች ሲጠቅም መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ቡድኑ ዘረፋና ህገወጥ ስራው ሲቀርበት ሀገር የማፈራረስ ስራ መጀመሩንም አስረድተዋል።
መንግስት ችግሮችን ለመፍታት በሆደ ሰፊነት ሲመለከት መቆየቱን የተናገሩት አስተዳዳሪው÷ ትዕግስት እንደፍርሃት የቆጠረው ወንበዴው ቡድን ባልታሰበ ሁኔታ ራሱን አሳልፎ በሰጠው ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረገሱን አንስተዋል።
በተሾመ ኃይሉ እና በአፈወርቅ እያዩ