Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ያሰማራቸው 242 ግለሰቦችና በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ትርምስ ለመፍጠር የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ያሰማራቸው 242 ግለሰቦችና በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፋት 5 ቀናት ውስጥ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

የጦር መሳሪያዎቹ በፍተሻ፣ በብርበራ እና በየስርቻው ተጥለው የተገኙ ናቸው ብለዋል።

በዚህም 18 ቦምቦች፣ 2 ፈንጂ፣ 1 ፀረ ተሽከርካሪ፣ 97 መገናኛ ሬዲዮ፣ 22 የትከሻ ሬዲዬ በፍተሻና በብርበራ የተያዘ መሆኑን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በተጨማሪም 2 ሺህ 686 የክላሽ ጥይቶች፣ 1 ሺህ 942 የሽጉጥ ጥይቶች፣  1 ጂ.ፒ.ኤስ፣ 4 የጦር ሜዳ መነፅር፣ 1 ላውንቸር፣ በአጠቃላይ 744 የጦር መሳሪያዎችና 4 ሺህ 628 ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

131 ሲምካርዶች፣ 6 የውጭ ስልክ መጥለፊያ፣ 74 የፀጥታ ደምብ ልብስ፣ 3 ሳይለንሰር፣ 600 ተንቀሳቃሽ ስልኮች መያዛቸውንም ገልፀዋል።

እንዲሁም የህወሓት ፅንፈኛ ያሰማራቸው 242 ግለሰቦች ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቅዋል።

ኮሚሽኑ ከፌዴራል ፖሊስና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ የህብረተሰቡ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በከተማዋ  ምንም አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት ከመጠበቁ በተጨማሪ መረጃና ጥቆማ በመስጠት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ በማምከን እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነር ጌቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በትዕግስት ስለሺ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.