የ4ኛ ሜካናይዝድ አዛዥ ሰራዊቱን በማታለልና ደባ በመስራት ጥቃት እንዲፈጸምበት የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል- የሰሜን እዝ አባላት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “የ4ኛ ሜካናይዝድ አዛዥ ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይ ሰራዊቱን በማታለልና ደባ በመስራት ጥቃት እንዲፈጸምበት የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል” ሲሉ ጥቃቱን ተከላክለው የተረፉ የሰሜን እዝ አባላት ተናገሩ።
“በፅንፈኛው የህወሃት ታጣቂ ሃይል የተፈፀመብን ጥቃት ከፍተኛ ክህደት ነው” ገልጸዋል።
ፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ አሳፋሪ ጥቃት ማድረሱ ይታወቃል።
የጁንታው ታጣቂ ሃይል በፈፀመው አስነዋሪ ድርጊት የእዙ አባላት ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም የአገር መከላከያ ሰራዊት ጥቃቱን መክቶ በፅንፈኛው ሃይል ላይ ህግ የማስከበር ተግባር እየፈፀመ ይገኛል።
ከፅንፈኛው ቡድን ጥቃት ተከላክለው የተረፉ የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዳሉት፥ የተፈጸመው ጥቃት በታሪክ ከፍተኛ ክህደት ነው።
ከሰሜን አዝ አባላት መካከል ፅንፈኛውን ሃይል በመከላከል የተረፉት አስር አለቃ ዋለልኝ ወርቅነህ እንደሚሉት፥ የአገር አለኝታ በሆነ ሰራዊት ላይ እንዲህ አይነት አስነዋሪ ተግባር የትም አገር ተፈፅሞ አያውቅም።
“በተለይ የ4ኛ ሜካናይዝድ አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይ ሰራዊቱን በማታለልና ደባ በመስራት የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል” ብለዋል
የጁንታው ቡድን ህይወቱን ለአገር አሳልፎ በሚሰጠው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በማድረስ ወደ ዝርፊያ መግባታቸውንም ተናግረዋል።
ጥቃቱ በተፈፀመበት እለት የሰሜን እዝ 4ኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይ የመከላከያ ሰራዊቱን መኪና ታርጋ በመቀየርና ሌሎች ተንኮሎችንም በመፈፀም አስጠቅተውናል ሲሉም ተናግረዋል።
በሰሜን እዝ 4ኛ ሜካናይዝድ 2ኛ ብርጌድ የብሬን ምድብተኛ ወታደር አዱኛ እምሩ የጁንታው ቡድን ምሽት ላይ ከበባ በማድረግ ያልታሰበ ጥቃት እንደሰነዘረባቸው አስታውሶ፤ ህወሃት ያስታጠቃቸው የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ከጁንታው ጋር ተባብረው ጥቃቱን እንደፈፀሙባቸውም ተናግሯል።
ከእዙ መካከል አስር አለቃ ወርቅነሽ ሰለሞንም የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በህወሃት ቡድን የተፈፀመው ክህደት የባንዳነት ተግባር መሆኑን ተናግራለች።
ሰራዊቱ ለትግራይ ህዝብ አንበጣን በመከላከል፣ ጤፍ በማጨድ፣ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት በመገንባት አገልጋይ እንደነበርም አስታውሳለች።
የሰራዊቱ አባላት ካላቸው ገንዘብ በማዋጣት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን ያስተምሩ እንደነበርም ገልጻለች።
“ነገር ግን በከሃዲው ቡድን በታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ክህደት ተፈፅሞብን ባጎረሰ እጃችን ተነክሰናል” ብላለች።
“ጁንታው የህወሃት ቡድን የፈጸመው አገርን የማፈራረስ አላማ የባነዳነት ድርጊት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያወግዘው ይገባል” ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።