Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች እንዲታገዱ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች እንዲታገዱ መወሰኑን የኢፌዴሪ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ፌዴራል ፖሊስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ አንዳንድ የግል የጥበቃ ኤጀንሲዎች የተቋቋሙበትን የመንግሥት እና የግል ተቋማትን የመጠበቅ ዓላማን ወደ ጎን በመተው ከቀጠሯቸው የጥበቃ አባላት መካከል ለሌላ እኩይ ተግባር የመረጧቸውን በመመልመል፣ ለተቋም ጥበቃ የተሰጣቸውን የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ እና በማሰማራት በሕዝብ እና በመንግሥት ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ አካላት ላይ ጥቃት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተደርሶበታል።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎቹ በቀጠሯቸው የጥበቃ አባላት እና ተባባሪዎቻቸው ባንኮችን እና የተለያዩ ድርጅቶችን ሲዘርፉ እና ሲያዘርፉ መቆየታቸውንም በአብነት ጠቅሷል።

በዚህም ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ እና ንብረት መዝረፋቸውን እና እንዲዘረፍም ማድረጋቸውን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ተቋማቱን እንዲጠብቁበት የታጠቁትን በርካታ የጦር መሣሪያ ይዘው እንደጠፉም ተረጋግጧል ብሏል።

እነዚህ ከተልዕኮአቸው ውጭ እንደሚንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች ይህም አልበቃ ብሏቸው አሁን ባለው ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ በጁንታው የሕወሓት ወንበዴ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈፀም የተለያዩ ግለሰቦችን ወደ ኤጀንሲዎቹ አስርገው በማስገባት እና የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ በኅብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ጥቃት ለመፈፀም እያሴሩ መሆኑ ነው ፌዴራል ፖሊስ የገለጸው።

በመሆኑም ከታች የተዘረዘሩት የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች፦

  1. ንስር የሰው ሃይል እና የጥበቃ አገ/ሃ/የተ/የግ/ማ
  2. አጋር የጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ
  3. ስብኃቱና ልጆቹ የንብረት አስ/ጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ
  4. ሰላም ሴኩሪቲ ሶሉሽን ኃ/የተ/የግ/ማ
  5. ኃይሌ ተክላይ እና ጓደኞቻቸው የጥበቃ አገልግሎት ህ/ስ/ማ
  6. ክፍሌ ጎሳዬ ሃጎስ እና ወ/ገብርኤል የጥበቃ አገልግሎት ሽርክና /ማ
  7. ዮናስ፣ ሮዛ እና መብርሂት የጥበቃ አገልግሎት ህ/ሽ/ማ
  8. ሃየሎም እና ብርሃኔ የጥበቃ አገልግሎት ህ/ሸ/ማ
  9. ደመላሽ፣ ሃፍቱ እና ጓደኞቻቸው የጥበቃ አገልግሎት ህ/ሸ/ማ
  10. ህሉፍና ሃለፎም የጥበቃ አገ/ህ/ሽ/ማ
  11. ዋልታ የጥበቃ የሰው ኃይልና ኮሚሽን ኃ/የተ/የግ/ማ
  12. ሴፍ የጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ
  13. አትላስ ጠቅላላ አገ/ኃ/የተ/የግ/ማ
  14. ጎህ የጥበቃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ

ለሀገር እና ለዜጎች ሰላም እና ደህንነት ሲባል ሥራቸውን እንዲያቆሙ የተወሰነና እስከአሁን ባለው ሀገር የማተራመስ እና ሕገ-ወጥ ሥራቸው በህግ የሚጠየቁ መሆኑን ገልጿል።

ስማቸው የተገለጸው የጥበቃ ተቋማት በአስቸኳይ ሥራቸውን አቁመው ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሪፖርት እንዲያደርጉም አሳውቋል።

በተጨማሪም ማንኛውም የግልም ሆነ የመንግሥት አካል ከነዚህ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች ምንም ዓይነት ቅጥር እንዳይፈፅም የተከለከለ መሆኑን አሳስቧል።

በመጨረሻም የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎቹ ስር ተቀጥረው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ያሉ ሠራተኞችን በተመለከተ ተገቢውን ልየታ በማድረግ ማስተካከያ እስኪወሰድ ድረስ በተመደቡበት ቦታ የጥበቃ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲሠሩ እና የሚጠብቋቸው የግል እና የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎችም በተሰጠው መግለጫ መሠረት ተገቢውን ቁጥጥር እና ክትትል እንዲያደርጉ ሆኖ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የጦር መሣሪያ ቁጥጥርና የግል ጥበቃ ተቋማት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ሪፖርት በማድረግ ቀጣይ በሚሰጡ የሥራ መመሪያዎች ብቻ ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.