Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ የትግራይ ህዝብና የፀጥታ አካላት ራሳቸውን ከስግብግቡ የህወሓት ቡድን እንዲያድኑ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ህዝብና የፀጥታ አካላት ራሳቸውን ከስግብግቡ የህወሓት ቡድን እንዲያድኑ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለትግራይ ህዝብና ለትግራይ የፀጥታ አካላት በትግርኛ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ቡድኑ በሁሉም ኣቅጣጫ ተከቦ መውጫ መግቢያ አጥቶ በጣረ ሞት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቡድኑ በየግንባሩ ተገኝቶ አመራር ሊሰጥ በማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የትግራይ ወጣቶችን ያለ ምግብና መጠጥ ለሞትና አካል ጉዳት እየዳረጋቸው እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

ስለሆነም የትግራይ ህዝብ ልጆቹን እየቀበረ ለሚገኘው ሃይል ሲል መስዋዕት ከመክፈል እንዲቆጠብና ፈጥኖ እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል።

“የትግራይ ህዝብ የልጆችህ ሞት የእኩዩን ቡድን እድሜ በሰአታት ወይም በቀናት ከማስረዘም በዘለለ የሚፈይደው የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሰው ለአላማ፣ ለሃገርና ለህዝብ እንጂ ለጥፋት ቡድን ብሎ መሞትና አካሉ መጉደል እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

አያይዘውም “የጁንታውን እድሜ በአጭሩ በመጨረስ ወደ ልማት ስራዎች እንድንመለስ ተባብረን መስራት ይገባልም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡

“የትግራይ ህዝብ የገነባሃትን ሃገር መልሰህ እንድታድናትና ታሪክህን እንድታድስም ሃገርህ ኢትዮጵያ ትጠራሃለች” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ልዩ ሃይልና የፀጥታ አካላትም ከቀናት ያልበለጠ ዕድሜ ለሌለው ቡድን ሲሉ ህይወታቸው እንዳያጡም ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ልዩ ሃይሉና የፀጥታ አካላቱ እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት በመስጠት በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ቀናት ራሳቸውን እንዲያድኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.