ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
እሾህ ነቅለን እሾህ የመትከል ህልምም ትልምም የለንም !
አላማችን ግፈኛውን ቡድን በመቅበር ተረኛ ግፈኛ ለመሆን አይደለም !
ለአማራ ክልል ህዝብና መንግስት !
በክልላችን ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች !
በአማራ ክልል ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች አንድ ናቸው። አንዳችን ለሌላችን መድሀኒት እንጂ ህመምም ሆነ የህመም ምልክት አይደለንም።
ወንበዴው ቡድን በሚያሰማራው አጥፊ ኃይል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሳንደናገጥ መደበኛ ኑሯችንን በወትሮ ዝግጁነት መምራት ይኖርብናል። የትግራይ ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከሁሉም የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተን ለጋራ አላማ በጋራ መስራት እንፈልጋለን።
ትህነግ የአማራም ሆነ የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ጠላት ነው። የታሪካዊ ግንኙነታችን፣ የአብሮነት ባህላችን፣ የጥንታዊና የመንፈሳዊ ቅርሶቻችን በአጠቃላይ የዘመናት ውህድ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ህጸጽ ነው።
ለትግራይ ተወላጆች ደህንነት ሲባል የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች ለጋራ ደህንነት የሚደረግ ጥበቃ ነው። የትህነግ ሴራ መጀመሪያ የሚያነጣጥረው በትግራይ ንጹሀን ዜጎች ላይ ነው።ስለሆነም የትግራይ ተወላጆችን በአማራና በኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ የወንድማማች መንፈስ እንጠብቃቸው። ስጋታቸውንና ጥርጣሬያቸውን በተግባር ስምሪት እናስወግድ።
የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ ብልጽግና ፅህፈት ቤት ኃላፊዎችና የክልል፣ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሁሉም የጸጥታ መዋቅርና መላው ህዝባችን ለደህንነታቸው ኃላፊነት መውሰድ ይገባናል። ለሚፈጠር ማንኛውም አይነት ችግር ታሪካዊና ህጋዊ ተጠያቂ መሆናችንን ተገንዝበን በየአካባቢያችን የሚኖሩ ተጋሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከአጥፊው የትህነግ ቡድንና የውስጥ ተላላኪዎች ሴራ እንጠብቃቸው።
በማንኛውም መንገድ ከወንድማማችነት ስሜት ባፈነገጠ መልኩ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ከወንበዴው ትህነግ ነጥለን የማናየው የአማራ ክልል ህዝብ ጠላት መሆኑን በአጽንኦት ለመግለጽ እንወዳለን።
የክልላችን የዴሞክራሲ ኃይሎች ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የማህበራዊ ድረ ገጽ ትስስር አንቂዎች፣ ምሁራን፣ የክልላችን ሴቶችና ወጣቶች ጥሪያችንን ተቀብላችሁ ለዜጎች ክብር በጋራ እንድንቆም በአማራነት ክብርና በኢትዮጵያዊነት ፍቅር ጥሪያችንን ስናቀርብላችሁ የጀመራችሁትን ህዝብ የማዳንና ሀገረመንግስት የማስቀጠል የትውልድ ተልዕኮ በድል እንደምትወጡ በመተማመን ነው።
የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ እናት ሁለት ጡቶች ናቸው።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት