Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የሚሰፍንበት እንጂ የአረመኔዎች እና የወንበዴዎች ዋሻ አትሆንም – የብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልጽግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ መግለጫ የሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የሚሰፍንበት እንጂ የአረመኔዎች እና የወንበዴዎች ዋሻ እንደማትሆን አስታውቋል፡፡

ሙሉ መግለጫው፡-

ሀገራችን ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የሚሰፍንበት እንጂ የአረመኔዎች እና የወንበዴዎች ዋሻ አትሆንም!!!

ከሀዲው የህወሃት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊታችን እና በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን የጭካኔ ተግባራት የሀገራችን ህዝቦች በሰላማዊ ሰልፎች እያወገዙት ይገኛሉ፡፡

መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አሸባሪው የጁንታው መሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ህዝባችን ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ሴረኛው ቡድን የፈፀመውን የሀገር ክህደት ወንጀል በውል ለማሳወቅ በሰላማዊ ሰልፎች መልዕክቱን አስተላልፏል እያስተላለፈም ይገኛል፡፡

ዛሬ ህዝባችንን ከዳር ዳር ያስቆጣው የሰው በላው ቡድን የጭካኔ ተግባር ለአመታት በህዝባችን ላይ ሲተገብረው የቆየዉ ጥንስስ ሴራ ነው፡፡

የባንዳው ቡድን በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የፈፀመው አሳፋሪ የሀገር ክህደት ወንጀል፤ከበረሃ የጀመረና ለእውነተኛ ትግል የወጡ ወንድሞቻቸውን በተኙበት መረሸን እና ንጹሃን ታጋዮችን በሴራ ወንጅሎ ማጥፋት እንዲሁም የትግል ጓዶቻቸውን በመክዳት እያደገ የመጣ የባንዳነት የልምምድ ውጤት ነው፡፡

ይህ የጥፋት ቡድን ከህዝባችን በዘረፈው ሀብት እንደ ኦነግ ሸኔ አይነት ጽንፈኛ ቡድኖችን አደራጅቶ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በማንነት ላይ ተመስርቶ ንጹሃን ዜጎችን በጭካኔ ጨፍጭፏል፡፡

በነዚህ ኢ-ሰብአዊ የጥፋት እቅዶች ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው በርካታ ንፁሀን ዜጎች በጅምላ ተገድለዋል፣ ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል፣ ህጻናት ያለአሳዳጊ፣ አዛውንቶች ያለጧሪ ቀርተዋል፡፡

በይበልጥ የህዝባችንን ቁጣ የቀሰቀሰና ኢትዮጵያን ያቆሰለ ጭፍጨፋ በዋና አጋሩ ኦነግ ሸኔ አማካኝነት በኦሮሚያ ምእራብ ወለጋ፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞኖች ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ የፈጀ ከመሆኑም በላይ ጨቅላ ህጻናትን፣ ነፍሰ ጡር ሴቶችን ሳይቀር ፍጹም ሰብዓዊነት በጎደለው ጭካኔ ገድሏል፡፡

የጥፋት ሀይሉ በተደጋጋሚ በንጹሃን ላይ ያካሄደው የእጅ አዙር ጭፍጨፋ ሀገር የማፍረስ እቅዱን ሊያሳካለት ባለመቻሉ ባሳለፍነው ሳምንት ጥቅምት 24/2013ዓ.ም የመጨረሻውን ቀይ መስመር አልፎ በሀገር ሉዋላዊነት ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ፈጽሟል፡፡

ይህ በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተፈጸመው አሳፋሪው ተግባር መላውን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጅግ ያስቆጣ እና የፈፀመው የሽብር ተግባር የለየለት ደም አፍሳሽ ወንበዴ ቡድን እንደሆነ በገሃድ አሳይቷል፡፡

ይሁን እንጂ እንኳን ለእናት ሀገር ከሀዲዎች በጠላት ወራሪዎች ያልተበገረው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን የነዚህን ጡት ነካሽ ጁንታ ቡድኖች እኩይ ተግባር ካመከነ በኋላ ዱካቸውን እየተከታተለ በፍጥነት ወደ መልሶ ማጥቃት ዘመቻ በመሻገር ባጭር ጊዜ ውስጥ ይህ የጥፋት ሀይል ለፈጸመው ሰይጣናዊ ተግባር ለፍርድ የማቅረቡን ስራ በንቃት እየሰራ ሲሆን በቅርቡ በድል ያጠናቅቃል፡፡

ከሀዲው የህወሓት ቡድን በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስትም ሀገራቸውን በካዱ ወንጀለኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዷል በመውሰድም ላይ ይገኛል፡፡

ይህ አረመኔ ቡድን ከዚህ ቀደም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በእጅ አዙር ሲፈጽመው የነበረውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ አሁንም በቀጥታ በራሱ የጭካኔ ተግባር ፈጽሞታል፡፡ ለአብነትም የጥፋት ሀይሉ በማይካድራ ከተማ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ ፈጽሟል፡፡

ይህ ብዙዎች ያለቁበት የጅምላ ጭፍጨፋ አላማና ግቡ በግልጽ የተለየ ነው፡፡ ጭፍጨፋው ከዚህ በፊት ህዝብን በህዝብ ላይ በማስነሳት በተለያዩ አካባቢዎች ሞክሮት ያልተሳካለት የጥፋት ሴራው አካል መሆኑን የሀገራችን ህዝቦች በውል ተረድተዋል፡፡

ስለሆነም አረመኔው ቡድን ለሀገራቸው ክብር መስዋእት ለመሆን የተዘጋጁ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከጀርባ በመውጋትና ንጹሃንን በመጨፍጨፍ የፈጸማቸው ወንጀሎች የህዝባችንን ስሜት ፈንቅሎ በቁጣ አደባባይ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡

ህዝቡ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በሰላማዊ ሰልፎች ከመጠየቁም ባሻገር መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ በተለያየ አግባብ እየደገፈ ይገኛል፡፡

ይህ የህዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በተለይም የነፍሰ በላው ቡድን ፍጻሜ እስኪጠናቀቅ በየአካባቢው ሊፈጥራቸው የሚችለውን እኩይ የጥፋት ሙከራዎች በመረዳት የፓርቲያችን አባላት፣ ደጋፊዎች እና መላ የሀገራችን ህዝቦች አካባቢያችሁን በንቃት በመጠበቅ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ፓርቲያችን ብልጽግና ይህን የጥፋት ቡድን ባጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብ የሚወስደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ ትኖራለች እንጂ አትፈርስም!

ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም
ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.